ሁሉም ት/ቤቶች ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ማስተማር ይጀምራሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከመጪው መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የዘንድሮው ዓመት የመማር ማስተማር ሥራ ይጀመራል።
ለ2018 የትምህርት ዘመን በየደረጃው ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉ ቁሳቁስን ጨምሮ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
በባለፈው ዓመት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ጨምሮ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ወላጆች፣ መምህራንና የዘርፉ ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ መቅረቡ የሚታወስ ነው።
ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር የሚገኝ ተማሪ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ታብሌትና የትኛውንም የትምህርት ሥራ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድርና አዋኪ የሆነ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስ ይዞ መገኘት ተከልክሏል፡፡
ከነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ የትምህርት ምዝገባ እና ተጓዳኝ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸው ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ7 ሚሊየን በላይ ሕጻናት በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፡፡
ወላጆች ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ልጅን ወደ ት/ቤት አለመላክ እንደሚያስጠይቅ አውቀው የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት እንዲወጡ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡