ሚኬል አርቴታ አማትሪያን…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል መሪ ሚኬል አርቴታ አማትሪያን የተወለደው በፈረንጆቹ 1982 በስፔን ሳን ሴባስቲያን ሲሆን፤ የእግር ኳስ ህይወቱ ጅማሬና ዕድገት በካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ነው፡፡
በባርሴሎና የታሰበውን ያክል የጨዋታ ጊዜ ባለማግኘቱ ወደ ፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴን ዠርመ በማቅናት 18 ወራትን በውሰት አሳልፏል፡፡
በእግር ኳስ ተጫዋችነት ጉዞው እንደሌሎች ስፔናዊያን የመሃል ሜዳ ሞተሮች መፍካት ባይችልም ለስኮትላንዱ ሬንጀርስ፣ ለስፔኑ ሪያል ሶሴዳድ እንዲሁም ለእንግሊዞቹ ኤቨርተንና አርሰናል ክለቦች ተጫውቷል።
በተለይም በመርሲሳይዱ ኤቨርተን በነበረው የስድስት ዓመታት ቆይታ በተጫዋችነት ዘመኑ ጥሩ ጊዜ አሳልፏል።
ለሀገሩ ስፔን በተለያየ የእድሜ እርከን ለታዳጊ ቡድን የተጫወተው ሚኬል አርቴታ፤ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድል አላገኘም።
በተጫዋችነት ዘመኑ ደምቆ መታየት ያልቻለው ሚኬል አርቴታ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።
በማንቼስተር ሲቲ ቤት የስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ረዳት በመሆን የአሰልጣኝነት ህይወትን በፈረንጆቹ 2016 የጀመረው አርቴታ፤ በኢቲሀድ በቆየባቸው ሶስት አመታት ሁለት የፕርሚየር ሊግ፣ አንድ የኤፍኤ እና ሁለት ካራባኦ ዋንጫዎች አንስቷል።
በ2019 የመድፈኞቹ አሰልጣኝ የነበሩት ስፔናዊው ኡናይ ኤምሪ ስንብትን ተከትሎ የሰሜን ለንደኑ ክለብ ሚኬል አርቴታን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን ይፋ አደረገ፡፡
በወቅቱ መድፈኞቹ የዝቅታ ዘመናቸው ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ሹመቱ ስህተት እንደነበር ብዙዎች ትችታቸውን ሰንዝረው ነበር፡፡
አርቴታ በወቅቱ በክለቡ ያለው የስራ ባህል ደካማ መሆኑንና ቡድኑ አቅጣጫ ማጣቱን በመግለጽ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ የተነሳሽነትና የፍላጎት ማጣት ችግር ነበረባቸው ያላቸውን በማሰናበት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ተጫዋቾችን እንደሚፈልግ በግል ተናገረ፡፡
በዚህ የማይስማሙ ተጫዋቾች ሊገነባ ለሚፈልገው የስራ ባህል እንቅፋት እንደሚሆኑበት በመግለጽ አብሮ ለመቀጠል እንደሚቸገር በድፍረት የተናገረው አርቴታ፤ በቅጥሩ የመጀመሪያው ዓመት የእንግሊዝ ኤፍኤ ዋንጫን በማንሳት ጅማሮውን አሳመረ፡፡
በዚህ ሂደት የወቅቱ የቡድኑ ኮከብ ተጫዋቾች የነበሩትን ሜሱት ኦዚል፣ ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግና ሌሎችንም ከቡድኑ ያስወጣበት መንገድ አነጋጋሪ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በአርቴታ ውጥን እምነቱን ያሳደረው የአርሰናል ቦርድ በክለቡ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ ሚሊየን ፓውንድ ፈሰስ በማድረግ ለአሰልጣኙ ድጋፉን አሳይቷል፡፡
መድፈኞቹ ከታሪካቸው በተቃራኒ የበይ ተመልካች ሆነውበት ወደ ነበረው ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ዳግም ተሳታፊ ብሎም ተፎካካሪ እንዲሆኑ ማድረግ የቻለው አሰልጣኙ፥ የሊጉ ተፎካካሪና ለዋንጫ ተገማች ቡድን በመገንባት ድንቅ የእግር ኳስ አዋቂ መሆኑን እያስመለከተ ይገኛል፡፡
ባለፉት ጥቂት አመታት በአርቴታ እየተመራ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያወጣው አርሰናል የሊጉን ዋንጫ ባለማሳካቱ ከፍተኛ ትችት ሲቀርብበት ቢቆይም በዚህ ውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ ለማሳካት ዓልሞ እየሰራ ነው።
ከ2022/23 የውድድር ዘመን ጀምሮ ባሉት ሶስት አመታት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አስልጣኙ ላይ ያለውን ጫና ከባድ እንደሚያደርጉበት በብዙዎች ዘንድ እየተገመተ ይገኛል፡፡
በየዓመቱ እየተሻሻለ የመጣው አርሰናል በ2025/26 የውድድር ዓመት 11ኛ ሳምንት ላይ ከማንቼስተር ሲቲ በአራት ነጥብ ከፍ ብሎ በ26 ነጥቦች ሊጉን እየመራ ሲሆን፤ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ላይ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ በባየርን ሙኒክ በግብ ክፍያ ተበልጦ ከምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የባለፉት ጥቂት ዓመታት ልምዶችን በማንሳት በዚህ የውድድር ዘመንም የፔፕ ጓርዲዮላው ማንቼስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ከኋላ በመነሳት ያነሳል የሚሉ ድምጾች ቢበራከቱም አርቴታና ሰራዊቱ ግን ብቸኛ አማራጫቸው ዋንጫውን የግላቸው በማድረግ 22 አመት የሞላውን የቡድኑ የዋንጫ ረሃብ ማስታገስ የቤት ስራ አለባቸው፡፡
አርሰናል በብዙ መመዘኛዎች ወደ ክፍታ ያመጣው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት የልሂቃን አሰልጣኞችን ጎራ ለመቀላቀል እየተጋ ነው።
በታክቲክ መረዳት ልህቀቱ፣ ጫናን በመቋቋም ብቃቱ እና ከመገኛኛ ብዙሃን ጋር ባለው መልካም ግንኙነት የሚወደሰው ሚኬል አርቴታ አማትሪያን በአርሰናል ታሪክ ረጅም ዓመታትን ያሰለጠነ ስምንተኛው አሰልጣኝ በመሆን ቀጥሏል፡፡
በአቤል ነዋይ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!