Fana: At a Speed of Life!

በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራች ሚኒስትር የሾመችው ሀገር…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አልባንያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራች ሚኒስትር በመሾም በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤዲ ራማ ሙስናን ለመታገል በሚል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰራች ሚኒስትር በካቢኔያቸው ማካተታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስሪት የሆነችው ሚኒስትር ‘ዲዬላ’ የሚል ስያሜ የተሰጣት ሲሆን፥ ‘ጸሀይ’ የሚል ትርጉም እንዳለው ተነግሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ባህላዊ ልብስ ለብሳ የምትታየውን ሚኒስትር ባስተዋወቁበት መልዕክታቸው፥ የጉቦና የእጅ ጥምዘዛ ማስፈራሪያዎች ስጋት የለባትም ነው ያሉት፡፡

የመንግስትን ስራዎች የሚያከናውኑ ተቋማትንና ኩባንያዎችን ለመምረጥ የሚከናወኑ ጨረታዎችን ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣት ሲሆን፥ የመንግስትን ስራዎች ቀልጣፋ ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እገዛ እንደምታደርግ ታምኖባታል፡፡

የኤ አይ ስሪቷ ሚኒስትር ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር በመተባበር የበለጸገች መሆኗን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ማሽኖች የሰውን የማሰብ ችሎታ የሚጠይቁ ተግባራትን እንዲፈጽሙ እያስቻለ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ እንዳለ ይነገራል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.