Fana: At a Speed of Life!

በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ታክስ ነጻ እንዲገቡ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ለአንድ ዓመት ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ ተፈቅዷል አለ የገንዘብ ሚኒስቴር፡፡

ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መግለጫ÷ ኢትዮጵያ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ የበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የዱር አራዊት፣ አእዋፍ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቦታዎች ሌሎች መልከዓ ምድሮች መገኛ ሀገር መሆኗን አንስቷል፡፡

መንግሥት እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች በተገቢው መንገድ በማልማት እና በማስተዋወቅ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንዲችሉ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡

ከቱሪስት መዳረሻዎቹ ውስጥ ከ20 በላይ ሐይቆች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ገልጾ÷ እነዚህ ሐይቆች በተገቢው መንገድ እንዲለሙ ቢደረግ ተጨማሪ መዳረሻ እና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚሆኑ ጠቅሷል፡፡

ሐይቆች የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም የገንዘብ ሚኒስቴር በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሞተር ኃይል የሚሠሩ ጀልባዎችን ለአንድ ዓመት ያህል ከማናቸውም ቀረጥ እና ታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያስችል መመሪያ አውጥቷል።

በዚህም መሠረት መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማናቸውም በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ ሰው ወደ ሀገር የሚያስገባቸው፦

Ø ፈጣን እና ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጡ ለዓሣ ማጥመጃ እና ለአጫጭር ርቀት የመንገደኛ ማጓጓዣ የሚውሉ አነስተኛ እና መካከለኛ የሞተር ጀልባዎች (outboard motor boats)፤

 

Ø በመካከለኛ ሐይቆች ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ፤ ለቱሪስት እና ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ፈጣን ጀልባዎች(speedboats)፣

 

Ø ለቱሪስቶች ጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ግልጽ ወይም በከፊል የተሸፈኑ  ጀልባዎች(Tourist excursion boats)፣

 

Ø ለሰዎች ማጓጓዣ የሚውሉ ጀልባዎች (Ferries)፣

 

Ø ለጥናት እና ምርምር የሚያገለግሎ ጀልባዎች(Research boats)፤

 

 

Ø ለግል አገልግሎት የሚውሉ ጀልባዎች (Private motor boats)፣

 

Ø በጸሐይ ኃይል እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ጀልባዎች( Eco boats)፣

 

Ø ጠፍጣፋ እና ባለ ጣሪያ የሞተር ጀልባዎች (pontoon boats)፣

 

እና የመሳሰሉት ለሀገራችን ሐይቆች ተስማሚ የሆኑ የሞተር ጀልባዎች ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር እንዲገቡ ተወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.