የባሕል ዲፕሎማሲ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ባህልና ጥልቅ ጥበብ ለማሳየት ያለመ የባሕል ዲፕሎማሲ መድረክ ዛሬ ማምሻውን በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ጨምሮ ሚኒስትሮችና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተለያዩ የባሕል ስራዎችና የጥበብ ክዋኔዎች ቀርበዋል፡፡
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) በዚሁ ወቅት÷ የ13 ወር ጸጋ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የፍጥረት መነሻና ዛሬም የሚወሱ የበርካታ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፥ አሁንም ታሪክ እየሰራች ቀጥላለች ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን ባህልና ጥልቅ ጥበብ ለማሳየት ያለመና ግንኙነትን እንደሚያዳብር ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መርቃ አዲስ ዓመትን በተቀበለችበት ማግስት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።
የባሕል ዲፕሎማሲ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም አውጥቶ ከመጠቀም አንፃር እየተሰሩ ላሉ ተግባራትም ማሳያ መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
በአሸናፊ ሽብሩ