Fana: At a Speed of Life!

 ሀምበሪቾ 777 የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን የሚገኘውን ሀምበሪቾ 777 በበርካታ መንገድ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ ነው አሉ።

በቱሪዝም ሚኒስትሯ የተመራ ቡድን  ዘንድሮ የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀንን በማስመልከት በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን እየጎበኘ ነው።

የጉብኝቱ ዓላማ ክልሉ ያሉትን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም ፀጋዎች በማስተዋወቅ፣ ምቹ መዳረሻ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የልማት ሥራዎችን ለመለየትና በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎችን ለመቃኘት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችን ለማቀድ መሆኑን ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።

የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስበው ሀምበሪቾ 777 የቱሪስት መዳረሻ ጎብኚዎችን በስፋት እንዲያስተናግድ ለማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል።

መስህቡ ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ትስስር በራሱ በበርካታ መንገድ የጎብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ የሚችል ዋነኛ የቱሪስት መስህብ መሆኑን ጠቅሰው፤ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ሀምበሪቾ 777 የሚገኝበት የሀምበሪቾ ተራራ በክልሉ ከምባታ ዞን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺህ 58 ሜትር ነው፡፡

የሀምበርቾ ኢኮ-ቱሪዝም ሥፍራ በአራት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ተራራውን የሚጋሩ 21 የገጠር ቀበሌዎችን የሚያቅፍ 18 ሺህ 604 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ቆዳ ስፋትን የያዘ ነው፡፡

 

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.