በአማራ ክልል የመስቀል ደመራ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ።
የጠቅላይ መምሪያው የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ፤ በቀጣይ የመስቀል ደመራ በዓልን ጨምሮ ሌሎች የአደባባይ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላትና ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት በሁሉም አካባቢዎች በዓሉ ያለምንም ችግር እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የመስቀል ደመራ በዓል የዕምነቱ ተከታዮችና በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የሚታደሙበት መሆኑን አንስተው፤ ለዚህ የሚመጥን የጸጥታ ዝግጅት መኖሩን ተናግረዋል።
ከጸጥታና ደኅንነት፣ ከሃይማኖት አባቶችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጭምር ከአጋር አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ መሆኑን ገልጸው÷ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት አጠራጣሪ ነገር ካጋጠመ ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የርችትና መሰል ነገሮችን መጠቀም በጥብቅ የተከለከለ መሆኑንም አሳስበዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን እገዛና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።