የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለተመዘገበው ደካማ ውጤት ይቅርታ ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተመዘገበው ደካማ ውጤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይቅርታ ጠየቀ፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን 20ኛውን የቶኪዮ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቆይታ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ አትሌቶች ለውድድሩ ጥሩ ዝግጅት ቢያደርጉም የተመዘገበው ውጤት የሚያስከፋ መሆኑን ተናግሯል።
ለዚህም የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን ብሏል።
በውድድሩ ወቅት እና ከውድድሩ አስቀድሞ በነበረው ዝግጅት በአትሌቶች እና በአሰልጣኞች መካካል ተከባብሮ ያለመስራት ችግር ሲስተዋል እንደነበር ተናግሯል።
የአትሌቶች በጋራ ልምምድ ለመስራት ፈቃደኛ ያለመሆን አንዱ የውጤት መጥፋት መንስኤ መሆኑን ጠቅሶ፤ ፌዴሬሽኑ እንደተቋም መስራት የነበረበትን ስራ በጊዜ ማጠር እና ተያያዥ ጉዳዮች በበቂ ሁኔታ አለመስራቱን ገልጿል።
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የስልጠና መንገዳችንን ዞር ብለን እንድናይ እና እንደ ፌዴሬሽን አሰራራችንን እንድንፈትሽ ያደረገ ነው ብሏል።
የፌዴሬሽኑ የፋሲሊቲ ዳይሬክተር አሰፋ በቀለ በበኩላቸው÷ አንዳንድ አሰልጣኞች ባስገቡት መርሀ ግብር መሠረት ፌዴሬሽኑ የአትሌቶችን የልምምድ ሂደት ቅኝት ለማድረግ ቢሄድም አሰልጣኞች በቦታው እንደማይገኙ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት 22ኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቋ ይታወቃል።
በዳንኤል እንዳለ