Fana: At a Speed of Life!

የፖሊስ ተቋማትን የማደራጀትና የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎የአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) የፖሊስ ተቋማትን ይበልጥ የማደራጀት፣ የማዘመንና የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ።

ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በክልሉ ደብረ ብርሃን ከተማ ልዩ ስሙ ካራፊኖ በሚባል አካባቢ የጀግኖች ማዕከል ግንባታን አስጀምረዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የፖሊስ ተቋማትን በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ ይበልጥ የማጠናከርና የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የፖሊስ አባላት የሚሰጡትን ህዝባዊ አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በዳበረ እውቀት እንዲሁም ክህሎት የታገዘ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

በዛሬው እለት የተጀመረው የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ለፖሊስ የሚሰጠውን የህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶች በማሳለጥ አባላት ብቁ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የፖሊስ ተቋማትን ይበልጥ የማደራጀት፣ የማዘመን እና የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንደሚቀጥልም ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ የከተማዋን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ፖሊስ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ለፖሊስ የላቀ አገልግሎትና ዝግጁነት የሚያስፈልጉ ነገሮችን የማሟላት ሥራ የጋራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለጀግኖች ማዕከል ግንባታ ከተማ አስተዳደሩ ቦታ ማመቻቸቱን አንስተው፤ ለግንባታው መሳካትም የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.