በቢሾፍቱ የሆረ ሃርሰዴ ኢሬቻ በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሆረ ሃርሰዴ ኢሬቻ በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው አለ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ፡፡
የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ኢብራሄም ሁሴን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ሁሉን ነገር ለፈጠረ አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው፡፡
የአንድነት፣ የፍቅር እና የወንድማማችነት በዓል የሆነው ኢሬቻ መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪ የሚለመንበት መሆኑንም አውስተዋል፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ የዘንድሮውን የሆረ ሃርሰዴ ኢሬቻ በዓል በድምቀት ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት እያጠናቀቀች ነው ብለዋል ሃላፊው፡፡
በዚህ መሰረትም በበዓሉ ለሚታደሙ እንግዶች በቂ መስተንግዶ ለመስጠት ሆቴሎችን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከተማ አስተዳደሩ የተዋቀሩ የጸጥታ አካላትም በዓሉ በድምቀት እንዲከበር አስተማማኝ ዝግጅት አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
ለሆረ ሃርሰዴ ኢሬቻ በዓል ወደ ቢሾፍቱ ለሚመጡ እንግዶች ባህላዊ እሴቱን የሚያንጸባርቅ አቀባበል እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
በኮሪደር ልማት እየተዋበች የምትገኘው ቢሾፍቱ በዓሉ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር የምታደርገው ሁለንተናዊ ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዓሉ የሚከበርበት ሆረ ሃርሰዴ አካባቢ አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራ የተከናወነለት መሆኑንም አቶ ኢብራሄም አስረድተዋል፡፡
በየዓመቱ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የንግድ ተቋማትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማነቃቃት ባለፈ የቱሪዝም መዳረሻነትን ከማስፋት አንጻር ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ስለሆነም የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ጎብኚዎች በሆረ አርሰዴ ኢሬቻ በዓል ላይ እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 24 ቀን በሆረ ፊንፊኔ እና መስከረም 25 ቀን ደግሞ በሆረ ሃርሰዴ “ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል፡፡
በመላኩ ገድፍ