የሀረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀረሪ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 5ኛ አመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ÷ አሁን ያለንበት ወቅት አዲሱ የለውጥ አመራር በርካታ ትላልቅ ስራዎችን እየሰራ ባለበትና የኢትዮጵያ ህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ሀገር የማሻገር ተግባራትን ለማደናቀፍ የሚሹ የጠላት ሀይሎች በርካታ ጥረት እያደረጉ ያለበት ነው ብለዋል።
በተለይም የነፃነት ታጋይ የሆነው ታዋቂው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በጥፋት ሀይሎች በማጣታችን በራሴና በሀረሪ ህዝብ ክልል ምክር ቤት ስም የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁም ነው ያሉት ።
ሆኖም መንግስትና ህዝብ በሚያከናውኗቸው የተቀናጀ ስራ ጸረ ሰላም ሃይሎች የሚያልሙት እኩይ ተግባር በየጊዜው እየከሸፈ እንደሚገኝም ገልጸዋል ።
በክልሉም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ አመራሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አንስተዋል።
ህብረተሰቡም በዚህ ወቅት በመደጋገፍና በመረዳዳት አንድነቱን ማሳየት እንደሚገባውም ተናግረዋል።
አያይዘውም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ በቀጣይም ስራዎቹን በቅንጅት ለመስራት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አውስተዋል።
ከዚህ ባለፈም የክልሉ መንግስት የጀመራቸው የልማትና፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የ2012 በጀት አመት አፈፃፀም ሪፖርትን አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ በ2 ቀናት ቆይታው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።