የግብር ክፍያ ስርዓትን በማዘመን የሌቦችን ቁጥር መቀነስ ተችሏል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብር ክፍያ ስርዓትን በማዘመን የሌቦችን ቁጥር መቀነስ ተችሏል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
የ7ኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሽልማት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የግብር ክፍያ አለመዘመን እና በግብር አከፋፈል የሚታየው ቢሮክራሲ ከግብር ከፋዮች ዘንድ ቅሬታ ይነሳበት እንደነበር አንስተዋል፡፡
የግብር ከፋዮችን ቅሬታ በመቀበል መንግሥት ባከናወናቸው ተግባራት ሀገር በቀል በሆኑ ፈጠራዎች በመታገዝ የግብር ክፍያ ስርዓትን ማዘመን እንደተቻለ ተናግረዋል።
በዚህም በግብር ቢሮክራሲ የሚገጥሙ ችግሮችን መቅረፍ እና የግብር መጭበርበርን መጠን መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ቃል ገብቶ እንደነበር አስታውሰው÷ በተሰበሰበው ግብር በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የኮሪደር ልማትን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የገባውን ቃል መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
መንግሥት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ በግብር ከፋዮች ሀገር እየተገነባች ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም የግሉ ሴክተር ከትርፍ በላይ ግብር በመክፈል ማህበራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡