Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማስተግበር በኩል ሰፊ ክፍተት አለ – አቶ ንጉሱ ጥላሁን

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትክክል በማስተግበሩ በኩል ሰፊ ክፍተት መኖሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሰክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል።
 
የጤና ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች ለተወከሉ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የኮሮናን ቫይረስ ስርጭት ለመግታት በአዲስ መልክ የተጀመረውን “ማህበረስብ አቀፍ ንቅናቄ እና የምርመራ ዘመቻ” ለማሳካት የሚያግዝ የስልጠና መድረክ በአዳማ ተሰጥቷል ።
 
በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሰክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን÷ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትክክል በማስተግበሩ በኩል ሰፊ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።
 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባደረገው ጥናትና የመስክ ምልከታ በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋትና በአስፈፃሚው አካል ባለው ቸልተኝነት አዋጁ መጣሱን ማረጋገጡንም ገልጸዋል።
 
የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች በሚጥሱት አካላት ላይ ለህዝብ ደህንነት ሲባል የእርምት እርምጃ በመውሰድ የባህሪ መጓደል ሁኔታዎች ማስተካከል አለብንም ብለዋል።
 
አያይዘውም አሁን እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ አካባቢ የሚታየውን የአስተምሮ መጓደል ማረም ይገባልም ነው ያሉት።
 
ስለ ቫይረሱ በማወቅና በመገንዘብ በህዝቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ጥሩ ቢሆንም ቫይረሱን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎች እየተተገበሩ አለመሆኑንም አስረድተዋል።
 
እስካሁን ቫይረሱን ለመከላከል የተከናወኑት ተግባራት የቫይረሱ ስርጭት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መርዳቱን የተናገሩት አቶ ንጉሱ÷ የነበረውን የአስተምህሮ ሂደት በመለወጥ በህብረተሰቡ ዘንድ የባህሪ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ስራ መጠናከር እንዳለበት አውስተዋል።
 
የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በበኩላቸው÷ ባለፉት ስድስት ወራት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ራሱን እንዲጠብቅ ከማድረግ አንፃር መገናኛ ብዙሀን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
 
ስልጠናው አሁን የተጀመረውን የምርመራና ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻ ግቡን እንዲመታ በሚደረገው ጥረት በሙያቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የተዘጋጀነው ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.