Fana: At a Speed of Life!

42 ዓመታትን ባሕር ላይ…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ካፒቴን ወዳጆ አሰፋ 42 ዓመታትን ባሕር ላይ ያሳለፉ መርከበኛ ናቸው፡፡

ካፒቴን ወዳጆ በልጅነታቸው መርከበኛ የመሆን ሕልም አልነበራቸውም።

ነገር ግን ተማሪ እያሉ የባሕር ኃይል አባላት የለበሱትን የደንብ ልብስ አይተው ቀልባቸው ወደ ሙያው መሳቡንና ወደ ሙያው መግባታቸውን ከፋና ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ወደ ሙያው በአጋጣሚ ይግቡ እንጂ ስራውን ወደው ሲሰሩ እንደቆዩ እና ከባሕር ውጪ ሌላ ሕይወት እንዲሁም ሌላ ስራ የመስራት ፍላጎት ኖሯቸው እንደማያውቅ ይገልጻሉ።

የ67 ዓመቱ ካፒቴን ወዳጆ አሰፋ ባለትዳር እና የሦስት ሴት ልጆች አባት ናቸው።

የስራ ባህሪያቸው ከቤት እንዲርቁ የሚያስገድዳቸው በመሆኑ ልጆቻቸው በሙሉ ሲወለዱ ከባለቤታቸው ጎን አልነበሩም፡፡

የመጀመሪያ ልጃቸው ተወልዳ 6 ወር ከሞላት በኋላ መጥተው ልጃቸውን እንዳዩ የሚናገሩት ካፒቴኑ÷ የመርከብ ሕይወት ጥሩ ነገር ቢኖረውም ለወራት ከቤተሰብ ርቆ መቆየት ትልቁ አሳዛኙ ነገር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የባሕር ላይ ሕይወት ገና ሲጀመር አስፈሪ ቢሆንም በሂደት እየተለመደ እንደሚመጣ በመግለጽ የባሕር ላይ ሕይወት ከተለያዩ አካባቢዎች ከሚመጡ ሰዎች ጋር የሚሰራ በመሆኑ መልካም ነገሮች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

በሀገር ውስጥ እንዲሁም በውጪ ሀገር የባሕር ኃይል ትምህርትን 8 ዓመት ከ8 ወር የተማሩት ካፒቴን ወዳጆ÷ ሩሲያ እና ጋና ከተማሩባቸው ሀገራት መካከል እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

በባሕር ላይ ሕይወታቸው ከአውሮፓ እና እስያ ሀገራት አብዛኞቹን በአፍሪካ ደግሞ የተወሰኑ ሀገራት ላይ እንደተጓዙም አብራርተዋል፡፡

በአንድ ወቅት ባሕር ላይ ባጋጠማቸው ማዕበል ምክንያት ከዚህ በኋላ አልሰራም እስከማለት ደርሰው የነበረ ቢሆንም ስራውን ማቋረጥ እንዳልቻሉ የሚገልጹት ካፒቴኑ÷ የባሕር ላይ ስራ ፅናት፣ ታታሪነት እና ትዕግስትን እንደሚጠይቅ አንስተዋል፡፡

መርከቡ ላይ ለተጫነው ነገር ኃላፊነት ስለሚኖር ዕቃውን ቦታው ላይ እስክናደርስ ድረስ እንጨነቃለን ነው ያሉት፡፡

አሁን ጡረታ ቢወጡም ሌሎች ተተኪ መርከበኞችን እያሰለጠኑ እንደሚገኙ ገልጸው÷ ኢትዮጵያዊያን በመርከብ ላይ እንዲሰሩ ብዙ መርከበኞችን የማፍራት ህልም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.