Fana: At a Speed of Life!

ሠንደቅ ዓላማና ሠራዊቱ ከቃል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የተገመደ ትስስር አላቸው – ጄ/ል ጌታቸው ጉዲና

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሠንደቅ ዓላማ እና መከላከያ ሠራዊት ከቃል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የተገመደ ትስስር አላቸው አሉ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና።

18ኛው ብሄራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ ሃሳብ በመከላከያ ሚኒስቴር ጠቅላይ መምሪያ ተከብሯል።

በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ በክብር እንግዳነት የተገኙት ጄ/ል ጌታቸው ጉዲና እንዳሉት ÷ ሠንደቅ ዓላማ እና መከላከያ ሠራዊት ከቃል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የተገመደ ትስስር አላቸው ።

የብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ከፍታ ከሀገራዊ ክብርና ማንነት ጋር በቀጥታ እንደሚቆራኝ አውስተው÷ የሀገር ክብር የሚረጋገጠውም ብሔራዊ ጥቅም በተሟላ መንገድ ሲጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

ታሪካዊ ጠላቶች በቻሉት ሁሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በመጻረር በእጅ አዙር የውስጥ ባንዳዎችን በማደራጀትና በመደገፍ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ከንቱ ምኞታቸው መክኗል ነው ያሉት።

ሠራዊቱ የተጣለበትን ሀገራዊ ጥቅም የማረጋገጥ አጀንዳ እውን ለማድረግ በሠንደቅ ዓላማ ሥር የገባውን ቃል ሊተገብር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ እና ሠራዊቷ ትብብር ወደ ከፍታ ዘመን ትሻገራለች ማለታቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.