Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ የምታራምደውን የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ውድቅ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ የምትከተለውን የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ የአፍሪካን የትብብር መንፈስ የሚጻረር እና ተቀባይነት የሌለው ነው ስትል ውድቅ አድርጋለች።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ÷ ግብፅ ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር በውሃ ፕሮጀክት ዘርፍ በትብብር እየሰራሁ ነው በሚል ያስተላለፈችው መልዕክት ፍጹም የተሳሳተና መሰረተ ቢስ ነው፡፡

ግብፅ በዓባይ ወንዝ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላትን ፀብ አጫሪ አቋም አጠናክራ መቀጠሏንም አመልክቷል፡፡

ከሰሞኑ የግብፅ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሀገሪቱ ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር በከርሰ ምድር ውሃ እንዲሁም በዝናብ ውሃ መሰብሰቢያ ፕሮጀክት ልማት ዘርፍ በትብብር እየሰራች እንደምትገኝና ለተፋሰሱ ሀገራት ድጋፍ እያደረገች እንደሆነ መግለጿን ጠቅሷል፡፡

በዚህም ግብፅ ከናይል ተፋሰስ ሀገራት የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ድጋፍ እንዳላት ለማሳየት መሞከሯን ነው ሚኒስቴሩ አጽንኦት የሰጠው፡፡

ግብፅ ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር ምንም አይነት የውሃ ፕሮጀክት ትብብር የላትም ያለው ሚኒስቴሩ ÷ በግብፅ ባለስልጣናት የተደረገው ንግግር ግን ግብፅ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያላትን የግንኙነት እውነታ ያዛባ ነው ብሏል፡፡

በውሃ ሃብት ልማት በትብብር ለመስራት የሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገራት የናይል ወንዝን በፍትሐዊነት የመጠቀም ይሁንታ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ÷ የግብፅ ምናባዊ የትብብር ፕሮጀክት ግን እውቅና እንደሌለው አስታውቋል፡፡

ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ባላት የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ በውሃ ሃብት ዘርፍ ትብብርን እና ዲፕሎማሲን ከመምረጥ ይልቅ ኢትዮጵያን የማፍረስ እና የማግለል የከሸፈ እና የተሳሳተ ፖሊሲ እየተከተለች እንደምትገኝ አስገንዝቧል፡፡

ላለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያና የናይል ተፋሰስ ሀገራት በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሕግ ማዕቀፍ ከግብፅ ጋር በትብብር ለመስራት ቢሞክሩም ግብፅ ግን በዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለመስማማት ፈቃደኛ ሳትሆን መቆየቷን መግለጫዋው አስታውሷል።

ግብፅ በዓባይ ወንዝ የውሃ ሙሌት እና የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ላይ ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት በተለየ ለሶስትዮሽ ድርድሮች ፊቷን አዙራ መቆየቷንም ጠቅሷል፡፡

85 በመቶ የዓባይ ወንዝ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በብልፅግና ጎዳና ላይ መሆኗን የገለጸው ሚኒስቴሩ ÷ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን የማልማት ተፈጥሯዊ መብቷን ማንም ሊከለክላት እንደማይችል አረጋግጧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.