Fana: At a Speed of Life!

ተማሪዎችን ለመቀበል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዝግጅት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በ2018 የትምህርት ዘመን አዲስ የተመደቡትን ጨምሮ እረፍት ላይ የቆዩ ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅቶችን ያደርጋሉ።
በዚሁም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡና የሪሚዲያል ትምህርት ለመውሰድ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የጅማ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራ ኃላፊዎች ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፍሬው አምሳሉ እንዳሉት÷ ተማሪዎች የሚመድቡበትን ማደሪያና የመማሪያ ክፍሎችን አስቀድመው በበይነመረብ ማየት እንዲችሉ ዩኒቨርሲቲው ዝግጅት አድርጓል።
ዩኒቨርሲቲው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውን የቤተሰብ ፕሮግራም ተሞክሮን በመውሰድ በዘንድሮው ዓመት ለመጀመር ከከተማው ነዋሪዎች እና ከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።
በሁሉም ትምህርቶች ላይ የተለያዩ የፕሮግራም ክለሳዎች እና ምልከታዎች እየተደረጉ እንደሚገኝ እና የተማሪዎች መግቢያ ቀንም በቅርብ ጊዜ እንደሚገለጽ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚመደቡለት ተማሪዎች ወደ ጅማ ከተማ ሲመጡ በከተማው አማካኝ ቦታ የትራንስፖርት አገልግሎት በማዘጋጀት ያለ እንግልት ወደየተመደቡበት ካምፓሶች እንዲገቡ ዝግጅት ማድረጉንም አንስተዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መሃመድ አህመድ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ለመቀበል የሚያስችለውን ዝግጅት ማከናወኑን እና የትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱን ለመደገፍ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት መጀመሩን አመላክተዋል።
የትምህርት ሂደቱ የተሳለጠ እንዲሆን 5 ሺህ ተማሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ቤተ መጻሕፍት በባለፈው ዓመት ገንብቶ ማስመረቁን የገለጹት ኃላፊው÷ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አልምቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን ተናግረዋል።
ተማሪዎች በቀላሉ በስልካቸው የትኛውንም መጽሐፍ መጠቀም እንዲችሉ ቤተመጻሕፍቱ በውስጡ 7 ሺህ መጻሕፍት ማካተቱንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት አካባቢ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት በመሆኑ ከማደሪያ ክፍሎች አንስቶ በቤተ መጻሕፍት እና የካፍቴሪያ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች ለይ የአየር ማቀዝቀዣዎችን በማስገጠም ለተማሪዎች ምቹ የትምህርት ከባቢን ለመፍጠር መሰራቱን አንስተዋል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.