Fana: At a Speed of Life!

ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ላላት የንግድ ትስስር ኢትዮጵያ ሁነኛ የመግቢያ በር ናት – ጃም ካማል ከሃን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፓኪስታን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ላላት የንግድ ትስስር ኢትዮጵያ ሁነኛ የመግቢያ በር ናት አሉ የፓኪስታን ንግድ ሚኒስትር ጃም ካማል ከሃን ፡፡

5ኛው የፓኪስታን አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባዔ እና ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና ሌሎች የተለያዩ ሀገራት ሚኒስትሮችን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የፓኪስታንና አፍሪካን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ባለመው ዓውደ ርዕይ ላይ ከ150 በላይ የፓኪስታን ኩባንያዎች እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት የዘርፉ ተዋናዮች ታድመዋል፡፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ምህዳር መፈጠሩን ጠቁመው÷ ለዚህም መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ስለሆነም የፓኪስታንን ጨምሮ የሌሎች ዓለም ሀገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጃም ካማል ከሃን በበኩላቸው÷ አፍሪካ አስደናቂ ሕዝብ እንዲሁም እምቅና ያልተነካ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት አውስተዋል፡፡

ፓኪስታን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በንግድ እና ሌሎች ዘርፎች ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክር ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ፓኪስታን በቀጣይ የዓለም የእድገት ማዕከል ከሆነችው አፍሪካ ጋር ላላት የንግድ ትስስር ኢትዮጵያ ሁነኛ የመግቢያ በር ናት ሲሉም አውስተዋል፡፡

ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር እና ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ለመተግበርም በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዓውደ ርዕዩ የሕክምና መድኃኒት ምርትና መሣሪያዎች፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች፣ የምግብና የምግብ ነክ የግብርና ምርቶች፣ የአውቶሞቲቭ መለዋወጫና ሌሎችም ምርቶች ቀርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.