Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ከበረሃ አንበጣና መሰል ስጋቶች ለመጠበቅ ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ከበረሃ አንበጣና መሰል ስጋቶች ለመጠበቅ ቁርጠኛ ናት አለ የግብርና ሚኒስቴር።

የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መቆጣጠሪያ ድርጅት ሚኒስትሮች ምክር ቤት 70ኛ ዓመታዊ ስብሰባ በኢትዮጵያ አስተጋጅነት ‘አስተማማኝ ድንበር ዘለል የሰብል ተባዮች መከላከል ሥራ ለቀጣናዊ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ’ በሚል መሪ ሐሳብ ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ ግብርናው ዋንኛ የኢኮኖሚ ምንጭ እና የአርሶ አደሩ መተዳደሪያ በመሆኑ ዘርፉን ከተለያዩ ስጋቶች ለመጠበቅ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ ናት።

የአፍሪካ ቀንድ በፈረንጆቹ ከ2019 እስከ 2021 በአንበጣ መንጋ መፈተኑን አስታውሰው፥ በዚህም የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መቆጣጠርያ ድርጅት ባከናወነው የተቀናጀ ተግባር ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።

ድርጅቱ ከምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር መስራቱ በቀጣናው ስጋት የሆነውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል እንዳስቻለም አመላክተዋል።

በዘርፉ የሚከሰቱ ችግሮች በአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን በቀጣናዊ ትብብርና ቅንጅት የሚፈቱ በመሆናቸው ሁሉም አባል ሀገራት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መቆጣጠሪያ ድርጅት ዳይሬክተር ሙዋሲንግዋ ሞሴስ ሪዋሄሩ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለድርጅቱ የሚጠበቅባት ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኗን አንስተዋል።

ድርጅቱ ድሮንን የመሳሰሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአባል ሀገራት የቅኝትና መከላከል ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ተቋሙ በቀጣናው እየተጫወተ ያለውን የበረሃ አንበጣን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ተባዮችን የመከላከል ስራ አባል ሀገራት በቁርጠኝነት እንዲደግፉት አስገንዝበዋል።

በቀጣናው ስጋት የሆነውን የአንበጣ መንጋ እና ግሪሳ ወፍ ለመከላከል መረጃ መለዋወጥ፣ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ እና ፋይናንስን በዘለቂነት አቀናጅቶ ማስኬድ አስፈላጊ እንደሆነ በመድረኩ ተጠቅሷል።

መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፥ በተቋሙ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.