ለአረንጓዴ አሻራ የተሰጠው ዓለም አቀፍ እውቅና ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ጉልበት ነው – ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተሰጠው ዓለም አቀፍ እውቅና ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታከናውናቸው የልማት ስራዎች ተጨማሪ ጉልበት ይሆናል አሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፡፡
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ)ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም በሚል ዘርፍ ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እውቅና መስጠቱ ይታወቃል።
ተቋሙ የሰጠውን የእውቅና ሽልማት በጣሊያን ሮም ተገኝተው የተቀበሉት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፥ ሽልማቱ ለኢትዮጵያውያን ተጨማሪ ጉልበት ነው ብለዋል፡፡
ፋኦ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ባከበረበት የዘንድሮው ጉባኤ ላይ ሀገራት እየተገበሯቸው የሚገኙና ከራሳቸው አልፈው ለዓለም ተምሳሌት ይሆናሉ ያላቸውን ስራዎች በልዩ ሁኔታ እውቅና መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ በተለይም በአካባቢ ጥበቃ፣ የተራቆተ አካባቢን መልሶ እንዲያገግም በማድረግና የስነ ምህዳር ጤናማነትን በማረጋገጥ ረገድ ያለውን አበርክቶ ከግምት በማስገባት ሽልማት እንደተበረከተላት ተናግረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሰፊ ሳይንሳዊ ምልከታዎች ተደርገውበት በርካታ መስፈርቶችን በማለፍ ለሽልማት መብቃቱን ነው ያስረዱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትውልድን ታሳቢ ያደረገና ከሀገር አልፎ ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፍ አበርክቶ ያለው መሆኑን ሲገልጹ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡
እውቅናው ዓለም ይህንን እውነታ መገንዘቡን አመላካች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመርሐ ግብሩ የተገኙ ልምዶች ለብዙ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆኑ በመድረኩ ላይ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተሰጣት ዓለም አቀፍ እውቅና ይህንን ስራ ለማገዝ የሚፈልጉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን ድጋፍ ለማሰባሰብ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ከልጅ እስከ አዋቂ ሚሊዮኖች የተሳተፉበት መርሐ ግብር እንደመሆኑ መጠን የተገኘው እውቅና ለኢትዮጵያውያን ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡