Fana: At a Speed of Life!

የሀምበሪቾ የሦስት ወራት ውጤት – 777 ደረጃዎችና 777 መረማመጃዎች

‎አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከምባታ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው።

ከከምባታ ሕዝብ ታሪክ ጋር የተያያዘው ሀምበርቾ ተራራ ከአዲስ አበባ 260 ኪሎ ሜትር፣ ከዞኑ ዋና ከተማ ዱራሜ ደግሞ በ8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝና 777 የመወጣጫ ደረጃ የተሰራለት ተራራ ነው።

የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የተራራው መወጣጫ ደረጃዎች ከሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሰባት ተራራዎች አንድ ላይ መሆናቸው፣ ከተራራው የሚፈልቁ ሰባት ምንጮች ሄደው አንድ ወንዝ መፍጠራቸውን እንዲሁም ሰባት ቀደምት የብሔረሰቡ ጎሣዎች በቦታው ላይ መስፈራቸውን ለማመላከት 777 ደረጃዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

በዚህም እጅግ ውብ ተፈጥሮን የታደለውና ከባሕር ጠለል በላይ 3 ሺህ 58 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ሀምበሪቾ ተራራ በአካባቢው ከሚኖረው ማሕበረሰብ ጋር እጅግ የተቆራኘ መሆኑን አመላክተዋል።

ቀደም ባለው ጊዜ ወደ ተራራ ለመውጣት ሰዎች እንደሚቸገሩ አስታውሰው፤ ከ2012 ዓ.ም ወዲህ በተሰራው 777 መወጣጫ ሕብረተሰቡ ተራራውን በመውጣት ጉብኝት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም የተራራው 777 መወጣጫ ጨርሰው ተጨማሪ 300 ሜትር ያህል ጎብኝተው እንደተመለሱ ዋና አስተዳዳሪው አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተራራው ላይ የተመለከቱትን የተፈጥሮ ደን፣ ተራራው አናት ላይ ያለውን አረንጓዴና ሜዳማ ስፍራ እንዲሁም ተጨማሪ ማራኪ ስፍራ አድንቀዋል።

የተሰሩ 777 መወጣጫዎች እነዚህን የመሳሰሉ ድንቅ ቦታዎች ለመጎብኘት በቂ ባለመሆናቸው ተጨማሪ መወጣጫ ደረጃዎች እንዲሰሩ ሐሳብ ሰጥተዋል።

በዚህም መነሻነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ለስራው የሚያስፈልግ ግብዓትና በጀት ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር የዞኑ ሕዝብ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ተጨማሪ የመወጣጫ ደረጃዎች መስራት ተጀምሮ በሶስት ወር ጊዜ ተጠናቋል።

በተሰራው ስራ ተጨማሪ 777 ደረጃዎች እንዲሁም 777 መረማመጃዎች ተሰርተው አጠቃላይ ደረጃዎቹና መረማመጃዎቹ ሦስት 777 መድረሳቸውን አመላክተዋል።

በዚህም ከዚህ በፊት ለመድረስ አዳጋች የነበረውን የሀምበሪቾ ተራራ መጨረሻ በመወጣጫ ደረጃዎች ሰው ሳይቸገር መድረስ እንደሚያስችል አቶ አረጋ አረጋግጠዋል።

አዲስ በተከናወነው የተራራ ልማት ቀደምት የከምባታ ሕዝብ አስተዳደርን (ሰጄ አስተዳደር) የሚያሳይ የቱሪስት መስህብ ስራ እንዲሁም ቀደምት የከምባታ መሪዎች መሃላ የሚፈጽሙበት “የኪዳን/መሃላ ድንጋይ (ህድር ክኒ)” ታሪካዊ ስፍራ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያ ጉብኝት ወቅት በድንገት ተገናኝተው በሽማግሌ የተመረቁበት ሥፍራ “ማሰ ክኑ” ምቹ የቱሪስቶች መስህብ የማድረግ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቅርቡ በስፍራው በመገኘት በተሰሩ ስራዎች ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ስራውን ለማከናወን በጥሬ ብር ወጪ የተደረገውን 16 ሚሊየን ብር ለመስጠት ቃል መግባታቸውንና ይህንንም ተጨማሪ ልማት በቦታው ላይ እንዲያከናውኑ ገቢ ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ብር ለጎብኚዎች ማረፊያ የሚሆኑ ቤቶች እንዲሰሩ ሐሳብ መስጠታቸውን ተከትሎ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግና በሌላ አቅጣጫ ወደ ተራራው በደረጃዎቹ መውጣት ለማይችሉ ጎብኝዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የ10 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሰው ኃይል በተከናወነው የተራራ ልማት ወጣቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረገው ሕብረተሰብ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.