በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለል ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጎ ፈቃድ በሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለል ተችሏል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
የ2017 ዓ.ም የከተማዋ የበጎ ፈቃደኞች የእውቅና መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ መንግስት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአቅመ ደካማ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።
በዚህም የማህበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ጠቅሰው፥ በከተማዋ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ በተለያዩ ዘርፎች በተሰማሩ ሙያተኞችና ባለሃብቶች በተከናወኑ አገልግሎቶች በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የሀገር እድገትንና የዜጎችን ዘርፈ ብዙ ጥያቄ በመንግስት ጥረት ብቻ መመለስ አዳጋች ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ የለውጡ መንግስት በቀረጸው ሰው ተኮር መርኃ ግብር አካታችና አሳታፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በጎ ፈቃደኝነትን በማስረፅ የተከናወኑ ተግባራት ጉልህ ፋይዳ እንደነበራቸው ያነሱት ከንቲባዋ፥ አሁን ላይ በጎ ፈቃደኝነት ባህል እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገር አንድነት፣ አብሮነትና መደጋገፍ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሳተፉ ወጣቶችና ባለሃብቶችን በማመስገን እውቅናው በቀጣይ ለሚያደርጉት ተሳትፎ መነቃቃትን ለመፍጠር ያለመ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡