Fana: At a Speed of Life!

ውጤት ያመጣው የሞሮኮ እግር ኳስ አብዮት…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ በእግር ኳስ አብዮቷ እና ስኬቷ ዓለምን እያስደነቀች ትገኛለች፡፡
ሀገሪቱ ባለፉት ቅርብ አመታት በወንዶች፣ በሴቶችና በታዳጊዎች እግር ኳስ እያሳየች ያለችው ስኬት አጀብ የሚያስብል ነው፡፡
በፈረንጆቹ 2022 የኳታሩ ዓለም ዋንጫ የሞሮኮ የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ፖርቹጋል እና ስፔን የመሳሰሉ የአውሮፓ ሀያል ብሔራዊ ቡድኖችን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜ በመድረስ ማነጋገሩ ይታወሳል፡፡
በዚህም ሞሮኮ በ2010 የደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫ የጋና ብሔራዊ ቡድን ሩብ ፍጻሜ በመድረስ ይዞት የቆየውን የአህጉሪቱን የስኬት ጣሪያ ማሻሻል ችላለች፡፡
በተመሳሳይ የሴቶች ብሔራዊ ቡድኗ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2023ቱ የዓለም ዋንጫ መሳተፍ የቻለ ሲሆን፥ በውድድሩ ጥሎ ማለፉን በመቀላቀል ስኬታም ጉዞ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በተለያየ የእድሜ እርከን የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖቿም በዓለም አቀፍ መድረክ ስኬት እያመጡ ይገኛሉ፡፡
ለአብነትም በቺሊ አስተናጋጅነት ሲካሄድ በቆየው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በፍጻሜው አርጀንቲናን 2 ለ 0 በመርታት ዋንጫውን ማሳካት ችላለች።
በዚህም ሞሮኮ ከጋና በመቀጠል ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫን ያሸነፈች ሁለተኛዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆን የቻለች ሲሆን፥ ሞሮኳዊው ያሲን ዛቢሪ በአምስት ግቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል።
ሞሮኮ አሁን ያለችበትን ስኬት ለማግኘት የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ከመገንባት ባለፈ ነባሮቹን በማደስ ውጤታማ ስራዎችን ሰርታለች፡፡
ሞሮኮ የእግር ኳስ ደረጃዋን ለማሻሻል ካከናወነቻቸው ስራዎች መካከል በፈረንጆቹ 2009 የሞሃመድ አምስተኛ የስፖርት አካዳሚን በ13 ሚሊየን ዩሮ መገንባቷ ተጠቃሽ ነው፡፡
አካዳሚው ታዳጊ ተጫዋቾችን በአዕምሮና አካል በማብቃት ረገድ ለሀገሪቱ እግር ኳስ እድገት አበርክቶው ወደር አይገኝለትም፡፡
የሞሮኮ እግር ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ መሻሻል ለማሳየቱ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው አካዳሚው፥ ዮሱፍ ኤል-ኔስሪ፣ ናይፍ አጓርድ፣ ሃምዛ ሜንዲል እና አዜዲን ኦናሂን የመሳሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾችን በማፍራት ለብሔራዊ ቡድኑ አብቅቷል፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኔዘርላንድ፣ ስፔን እና ፈረንሳይ የተወለዱና የዘር ሀረጋቸው ከሞሮኮ የሚመዘዙ ተጫዋቾችን በማሳመን ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን እንዲጫወቱ ማድረግ ችሏል፡፡
ሶፍያን አምራባት፣ ሃኪም ዚያች፣ ኖርዲን አምራባት፣ አሽራፍ ሃኪሚ እና ኑሰይር ማዝራዊ በዚህ ሂደት የሚጠቀሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
በጠንካራ ፕሮጀክት፣ በረጅም ጊዜ እቅድና ጠንክሮ በመስራት አሁን ላይ ሞሮኮ በእግር ኳሱ ትልቅ ስም ያላት አፍሪካዊ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡
የሀገሪቱ መንግስት በተለይም በታዳጊዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በእግር ኳሱ ላይ ያካሄደው ኢንቨስትመንት ባለፉት ዓመታት ለተገኘው ስኬት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
ሀገሪቱ የደረሰችበት የስኬት ደረጃና ለዚህ ስኬት የበቃችበት ሂደት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት እግር ኳሳቸውን ለማሳደግ ትልቅ ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.