ከ13 ሚሊየን በላይ የመኝታ አጎበር…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት ከ13 ሚሊየን በላይ የመኝታ አጎበር ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን ለፋና ፖድካስት እንዳሉት÷ ባለፉት ሶስት ወራት 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የወባ በሽታ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
ምርመራ ከተደረገባቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች በሽታው እንዳለበቸው መረጋገጡን አንስተው÷ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የታማሚዎችን ቁጥር ከ40 እስከ 49 በመቶ ያህል መቀነሱን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ የወባ በሽታ ስርጭት ሁኔታና መጠኑን በማጥናት ለመከላከል አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምርመራና ህክምናውን ጨምሮ የመድኃኒትና ግብዓት ተደራሽነትን በማሟላት ብሎም ያልተቆራረጠ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 177 ወረዳዎችን የሸፈነ የኬሚካል ርጭት መደረጉን አስታውሰው÷ በዚህ ዓመት በ217 ወረዳዎች 3 ሚሊየን ቤቶች ላይ ርጭት ለማድረግ ግብዓት መሰራጨቱንና በአብዛኛው ቦታ ላይ ርጭት መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ወባ የሕብረተሰብ ጤና ችግር እንዳይሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ዶ/ር ሕይወት÷ ከክረምት በኋላ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስና ሌሎች መከላከያ ተግባራትን ማጠናከር እንዲሁም በሽታ ከተከሰተም በአግባቡ ህክምና መውሰድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻዎች ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን በተደራጀ መልኩ የመከላከል ስራውን እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቅደስት ዘውዱ