Fana: At a Speed of Life!

የጤና ዘርፍ ሠራተኞች የማህበራዊ ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ዘርፍ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ የሚያደርግ የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ትግበራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ እንዳሉት ÷ጤናማና አምራች ዜጋ በመፍጠር የሀገርን እድገት እውን ለማድረግ በርካታ ስትራቴጂዎችና ሪፎርሞች ተቀርጸው እየተተገበሩ ነው ፡፡

ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ለማሳካት እንዲቻል ከተቀረጹ የተለያዩ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የጤና መድኅን አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ ለተሰማሩ ዜጎችና ለጡረታ ባለመብቶች የማህበራዊ የጤና መድኅን እንዲሁም መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ለተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርዓት መቀረጹን አመልክተዋል፡፡

የማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርዓትን ወደ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋፋት በ2017 ዓ.ም ከ13 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ እማ/አባወራዎች አባል ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከ63 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የጤና መድኅን ሽፋን መስጠት የተቻለ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ የ19 ሚሊየን ዜጎች ዓመታዊ የአባልነት መዋጮ በመንግሥት መሸፈኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ ለተሰማሩ ዜጎችና የጡረታ ባለመብቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረጸው የማህበራዊ የጤና መድኅን ሥርዓት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም የጤናው ዘርፍ የመንግሥት ሠራተኞች በስራቸው ባህርይ ምክንያት የጤና እክል ሲያጋጥማቸው የሕክምና አገልግሎት ወጪያቸው በመንግሥት ተሸፍኖ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም አዲስ በወጣው የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1363 ላይ የጤና ዘርፍ የመንግሥት ሠራተኛ የጤና መድኅን አባልነት ሙሉ መዋጮ በመንግስት እንዲሸፈን ተደንግጓል ነው ያሉት።

ስለሆነም በአዋጁ መሰረት በጤናው ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩ የመንግሥት ሠራተኞች የማሕበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አብስረዋል፡፡

ትግበራውን ደረጃ በደረጃ በማስፋት ሁሉም የመንግስት ሠራተኞች እና የጡረታ ባለመብቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚደረግም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.