Fana: At a Speed of Life!

ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው አሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ በብራሰልስ በተካሄደው የ2025 ግሎባል ጌትዌይ ፎረም ካደረጉት ተሳትፎ ጎን ለጎን ‘ዲፕሎማቲክ ወርልድ’ ከተሰኘው መጽሄት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ግድቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ከመሆን ባለፈ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋ የሰነቁበት እንዲሁም ኢትዮጵያ እንዳትለማ ማነቆ ከነበሩ ችግሮች የምትወጣበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከናይል ውሃ 85 በመቶ ያህሉ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ቢሆንም፥ አብዛኛው ህዝባችን መሰረታዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ሳይችል ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ በዚህ አግባብ የሚቀጥሉበት ምክንያት እንደሌለ አጽንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ይህንን ዘመናትን የተሻገረ ኢፍትሃዊነት የሻረ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሏን አስታውሰው፥ ሆኖም እድገቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይቀጥል በቂ የኃይል አቅርቦት አለመኖሩ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ግድቡ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት በእጥፍ የሚያሳድግ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት ጠንካራ መሰረት እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

ግድቡ የካርበን ልቀትን በመቀነስ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት የምትከተለውን ስትራቴጂ የሚደግፍና ችግሩን ለመቋቋም የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለቀጣናው ሀገራት ኃይል ለማቅረብ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ የቀጣናዊ ትብብርና የጋራ ልማት የማዕዘን ድንጋይ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ኬንያ እና ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች ሲሆን በተመሳሳይ ለታንዛኒያም ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆኗን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚያጠናክርና በቀጣናው የጋራ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በተለይም ግድቡ የተፋሰሱን ሀገራት ከከባድ የጎርፍ አደጋዎች በመከላከልና የመስኖ ልማት አቅምን በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ንጹህና በቂ የኃይል አቅርቦት መኖሩ በቀጣናው ኢንዱስትሪን በማስፋፋት ኢንቨስትመንትን ያጠናክራልም ነው ያሉት፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.