ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባን ብዝኀ መልክ ያሳያል – አቶ አድማሱ ዳምጠው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ በሚዲያ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የከተማዋ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሥራ ኃላፊዎች ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን የጎበኙ ሲሆን÷ የሁለቱ ተቋማት ማኔጅመንት አባላት በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው እንዳሉት፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ከተማ እንደመሆኗ ፋና በውስጧ ያቀፈችውን ብዝኀነት ከማጉላት አንጻር እየሰራ ይገኛል።
የመዲናዋ አስተዳደር ከተማዋ እንደ ስሟ አዲስ እና ውብ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን በሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ ሚዲያችን ግንባር ቀደም ሚናውን ይወጣል በማለት ገልጸው፤ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መዲና እንደመሆኗም ኃላፊነታችን ድርብ ነው ብለዋል፡፡
ይህንንም ከብሔራዊ ጥቅም፣ ከሀገራዊ ብልጽግና እና ከኢትዮጵያን ከፍታ አንጻር እየተነተነ መስራቱን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር በዚህ ወቅት÷ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባን ገጽታ በመግለጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አንስተዋል፡፡
በተለይም በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን እንዲሁም ከተማ አቀፍ ሁነቶችን የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ለከተማዋ ሁለተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በሚዲያ ዘርፍ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የይዘት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አልዓዛር ታደለ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በትብብር ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት አድንቀዋል።
ተቋማት ከሚዲያ ጋር ተቀራርበው ሲሰሩ በርካታ ችግሮች እንደሚፈቱም ተናግረዋል።
በመዲናዋ በርካታ ለሚዲያ የሚሆኑ ይዘቶች በመኖራቸው በቅንጅት መሥራታችን የያዝነውን ግብ ለማሳካት ያስችለናል ብለዋል።
በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሸለመ ከቤ÷ ቢሮው ፋና ለሚሰራቸው ዘገባዎች ቀና ትብብር ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲናም ጭምር ናት በማለት ገልጸው÷ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሁሉም የሚዲያ አማራጮቹ የሚሰጠውን የዘገባ ሽፋን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዘውዱ ከበደ፤ ከፋና ሚዲያ ጋር በትብብር መስራታችን የመዲናዋን የልማት፣ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ውይይቱን ተከትሎ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ በሚዲያ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ