Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ባንክ በግል እና ሶስተኛ ወገን የባንክ ሒሳብ አጠቃቀም ዙሪያ ጥብቅ መመሪያ አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በግል እና ሶስተኛ ወገን የባንክ ሒሳብ አጠቃቀም ዙሪያ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል።

ባንኩ ባደረገው ምርመራ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የባንክ ደንበኞች በዋናነት የንግድ ድርጅቶችና ግለሰብ ነጋዴዎች ካስመዘገቡት የባንክ ሒሳብ ውጪ የሶስተኛ ወገን የባንክ ሒሳብ በመጠቀም ግብይት እንደሚፈጽሙ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

በዚህም የተለያዩ የንግድ ግብይቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እየፈጸሙ መሆናቸውን ጠቁሟል።

ይህ አሰራር ከግብር ሰብሳቢ ባለስልጣናት ቁጥጥርና ክትትል ለመሸሽ የሚደረግ ተግባር ከመሆኑ በተጨማሪ በዚህ አግባብ የሚፈጸሙ የፋይናንስ ግብይቶችና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች የወንጀል ፍሬ ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ጋር የተያያዙ ወይም የተገናኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላክቷል፡፡

በመሆኑም እነዚህን መሰል ተግባራት ለመግታት አስፈላጊው የተቀናጀ ርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን ባንኩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነትና ታማኝነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ደህንነት ለመጠበቅ ለሁሉም ባንኮች የግል ባንክ ሒሳቦችን ለንግድ እና ሕገወጥ ድርጊት የሚጠቀሙ ደንበኞችን አስመልክቶ አስፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀት እንዲልኩ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.