የባሕር በር ባለቤትነታችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለን – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ባለቤትነታችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለን አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
118ኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን “የማትደፈር ሀገር የማይበገር ሠራዊት” በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ኃይል ማሰልጠኛ ት/ቤት እየተከበረ ነው።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ÷ ሀገራችን የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች አሉ ብለዋል።
በእነዚህ ጠላቶች ሴራ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ግጭት ላይ እንድታተኩርና ለዘመናት በድህነትና ኋላቀርነት እንድትቆይ መደረጓን አስገንዝበዋል፡፡
በሠራዊታችን ጀግንነት፣ በሕዝባችን ድጋፍ እና በመሪዎቻችን በሳል አመራር ሰጭነት ሴራውን በመበጣጠስ ወደ ሰላምና ልማት እየተሸጋገርን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይም የታሪካዊ ጠላቶቻችን እና የባዕዳን አቤት ባይ ኃይሎችን እኩይ ሴራ በማክሸፍ የልማት፣ የሰላምና የመንሠራራት መንገዳችንን ጀምረናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሞከሩ ኃይሎች ፈርሰው፤ የሀገር እና የተቋማት ሁለንተናዊ አቅም እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ነፃነቷና ሉዓላዊነቷ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር በርካታ መስዋዕትነት መከፈሉን አስታውሰዋል፡፡
ላለፋት 30 ዓመታት ተኝተናል፤ አሁን ግን ላንተኛ እንደሀገር ነቅተናል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ የሀገራችን የሕልውና ጥያቄ የሆነውን የሰላም ፣ የልማትና የባሕር በር ተጠቃሚነት እናሳካለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በማጠናከር ሰላማችን እና የባሕር በር ባለቤትነታችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለን ማለታቸውንም የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።