የኮሪደር ልማት ሥራ ለዜጎች ምቹ የአኗኗር ዘይቤን እየፈጠረ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ተጨማሪ ገጽታ እና ውበት ሰጥቷል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር የተጠናቀቀውን የሳር ቤት- ጀርመን አደባባይ-ጋርመንት እና ፉሪ አካባቢ የኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ ወቅት ÷ የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለዜጎች ምቹ የአኗኗር ዘይቤ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራው ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ገጽታ እና ውበት መስጠቱን ነው የገለጹት፡፡
ሥራው የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ፣ መንገዶችን ለእግረኞች ምቹ በማድረግና የተገነቡት ሱቆች ለዜጎች የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በኮሪደሩ የሚገኙ ከ20 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ስፖርቱን ለማሳደግና ትውልድን ለመቅረጽ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ከታች ጀምሮ በትውልድ ላይ እየሰራ መሆኑ በግልጽ የታየበት እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡