ከሞተር ሳይክል ማጠብ እስከ ተሽከርካሪ አስመጪነት…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ተወላጅ የሆነው ወጣት ሳዳም አብዳ ከ12 ዓመታት በፊት በ10 ብር ክፍያ ነበር የሞተር እጥበት ስራውን የጀመረው።
በወቅቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ማሕበር በመደራጀት ባገኘው 5 ሺህ ብር ስራውን የጀመረው ወጣቱ÷ በትጋት በመስራት ወደ ተሽከርካሪና ሞተር ሳይክል አስመጪነት መሸጋገሩን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ኮሌጅ በመግባት በአውቶሞቲቭ የትምህረት ዘርፍ ተምሮ በከፍተኛ ውጤት መመረቁን የሚገልጸው ወጣት ሳዳም÷ ትልቅ ዓላማ ሰንቆ በመነሳት ከምርቃቱ በኋላ በጊኒር ከተማ የሞተር ሳይክል እጥበት ስራውን እንደጀመረ አስታውሷል።
ቀስ በቀስም ስራውን ሞተር ሳይክል ወደ መጠገን በማሳደግ ከዓመታት በኋላ የሞተር መለዋወጫና አሮጌ ሞተር ሽያጭ ስራ ላይ በመሰማራትና በትጋት በመስራት ወደ ተሽከርካሪ መለዋወጫ መሸጫ ማሸጋገሩን ገልጿል።
በዚህም በጥቂት ዓመታት ወስጥ የተለያዩ ዘመናዊ ሞተር ሳይክሎችን በማምጣት ሽያጭ እንደጀመረ በመግለጽ÷ በሂደትም ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ መለዋወጫና ሞተር ሳይክሎችን ከውጭ ሀገር በስፋት እያመጣ መሸጥ መጀመሩን ጠቁሟል።
ከ5 ዓመታት በፊት ጀምሮ ከሞተር ሳይክል አስመጭነት በተጨማሪ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት የንግድ ሥራውን እንዳሳደገና በጊኒር ከተማ የጀመረውን ስራ በተለያዩ ሰባት ከተሞች ላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጸው።
አሁን ላይ ከራሱ አልፎ ከ230 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል እንዲሁም በጊዜያዊነት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችሏል።
በቀጣይም ስራውን በማሳደግ ወደ ተሽከርካሪ ማምረቻነት ለመሻገር ወጥኖ እየሰራ መሆኑን ይናገራል።
ማንም ሰው ዓላማውን ማሳካት ከፈለገ የስራ ባህሉን ማሳደግ፣ ስራን ማክበር፣ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀምና የተግባር ሰው ሊሆን እንደሚገባም ሐሳቡን አጋርቷል።
ወጣቱ ድጋፍ ላደረገለት ማሕበረሰብ የምስጋና መርሐ ግብር ያዘጋጀ ሲሆን÷ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሀመድ አብዱልቃድር አቶ ሳዳም ለወጣቱ ምሳሌ የሚሆንና ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግለት አረጋግጠዋል።
ከዚህ ቀደም ለተሽከርካሪ መገጣጠሚያ መክፈት የሚያስችል 5 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ በማግኘት ስራውን ለመጀመር የግንባታ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
አቶ ሳዳም በታማኝ ግብር ከፋይነት 900 ሚሊየን ብር በመክፈል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተከታታይ ሦስት ዓመታት እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል።
በብርሃኑ በጋሻው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!