Fana: At a Speed of Life!

ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንም ፈለገም አልፈለገም እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በ30 ዓመት ትግል በብዙዎች ርብርብ የባሕር በር ማጣቷን አስታውሰው፤ በተረጋጋ፣ በሰከነ መንገድ በውይይት የባሕር በር ማግኘት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ድንበርተኝነት ያሳጣው ውሳኔ በማን እንደተወሰነ የሚያሳይ ምንም አይነት የሰነድ ማስረጃ እንደሌለ ገልጸው፤ ውሳኔው ሕጋዊ እንዳልሆነ አንስተዋል።

ጉዳዩን መጠየቅ እና ማንሳት ነውርና ትክክል ያልሆነ አድርጎ የሚመለከት ትርክት እንዳለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባሕር እንደሚያስፈልጋት እና ከኤርትራ ጋር ሰላም በተፈጠረበት ወቅት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በሚሊኒየም አዳራሽ ማንሳታቸውን አስታውሰው፤ ወደ ኤርትራ በተጓዙበት ወቅት ወደብ ዋነኛ ጉዳይ እንደነበር ገልጸዋል።

በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ላይ ጂኦፖለቲካውን በመጻፍ ለኤርትራ ባለስልጣናት በስጦታ መልኩ እንደላኩላቸው ገልጸው፤ በቀይ ባሕር ላይ ለማሰማራት የባሕር ኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።

ከኤርትራ ጋር በመስማማት ወደብ ለማልማት ሙከራ ቢደረግም በኤርትራ መንግስት በኩል ትብብር የማድረግ ፍላጎት እንዳልነበረ ጠቅሰዋል።
አሰብን ለማልማት በየጊዜው ንግግር ቢደረግም ከኤርትራ መንግስት በኩል ግልጽ ባልሆነ መንገድ ለጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ አልነበረም ነው ያሉት።

ከኤርትራ ሕዝብ ጋር በጋራ መስራት ፍላጎታችን ነው፤ በፍጹም የመዋጋት ፍላጎት የለንም፤ በሕጋዊ እና በንግግር ሊፈታ የሚችል እምነት አለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን አንስተው፤ ቅድሚያ የምንሰጠውም ሰላም እና ንግግር ስለሆነ ሀገራት መፍትሔ እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ እንደማትኖር እርግጠኛ ነኝ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትልቅ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ስታድግ ሌሎችን የምታግዝ እንጂ ስጋት እንደማትሆን አረጋግጠዋል።

ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው ችግር ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጋር መያያዙን ጠቅሰው፤ ህወሃት እና ትግራይ ጨርሰው ካልጠፉ የሚል ፍላጎት በመኖሩ የመጣ እንደሆነም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.