Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ አሁን ላይ እዳዋን ለመክፈል ምንም ችግር የለባትም- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከሪፎርሙ ወዲህ በተሰሩ ስራዎች አሁን ላይ እዳዋን ለመክፈል ምንም ችግር የለባትም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አፍሪካ ውስጥ ከ1 እስከ 3ኛ ደረጃ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ እዳ አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ ያለባት እዳ 23 ቢሊየን ዶላር ገደማ መሆኑን ጠቅሰው፥ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ብዙ መክፈል በሚጠይቅ የብድር ስርዓት የተወሰደ በመሆኑ የብድር ሁኔታው እንዲሸጋሸግ መንግስት ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ከ4 እስከ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የእዳ ሽግሽግ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም የሪፎርሙ ውጤት የሆነ ታላቅ ድል መሆኑን አውስተዋል፡፡

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አጀንዳ በብዝሃ ዘርፍና ብዝሃ ተወናይ ታግዞ መመራት አለበት በሚለው እሳቤ መሰረት ምቹ የኢንቨሰትመንት ከባቢን ለመፍጠር ዘርፉን ዘመናዊና አካታች ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማረቅ እንደመሆኑ መጠን መንግስት የተረከበውን ከፍተኛ ዕዳና የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት መጠገን ችሏል ነው ያሉት፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት በማጠናከር፣ የወጪ ንግድን በማሳደግና የተጠናከረ የፋይናንስ ስርዓት በመዘርጋት ረገድ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን በቴክኖሎጂ በማዘመን በተሰሩ ስራዎች በለውጡ ወቅት 170 ቢሊየን ብር የነበረው የመንግስት ገቢ በዚህ ዓመት አንድ ትሪሊየን ብር ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

የእዳ ጫናን ለመቀነስ ጥረት ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እዳዋን ለመክፈልና ለማስተዳደር ምንም ችግር እንደሌለባት ተናግረዋል፡፡

ገቢን ለማሻሻል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ራሱን የቻለ ሪፎርም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሙ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል።

ከወጪ ንግድ ዘርፍ ሪፎርም አስቀድሞ በ2016 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ ለውጭ ገበያ የቀረበውን ያህል ምርት በዚህ ዓመት በ4 ወር ብቻ ወደ ውጭ መላክ መቻሉን አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.