2ኛው ምዕራፍ የጋዝ ልማትና የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች በ2 ዓመት ይጠናቀቃሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቅርቡ የጀመረቻቸው 2ኛው ምዕራፍ የጋዝ ልማትና የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች በ2 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃሉ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ በሶማሌ ክልል ውስጥ 21 ትሪሊየን ኪውቢክ ጫማ የጋዝ ክምችት መኖሩ በሦስተኛ ወገን ተረጋግጧል።
ይህ በአንድ ቦታ የተገኘው የጋዝ ክምችት ትልቅ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፥ በተመሳሳይ ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም በተለይ በነዳጅና ወርቅ ልማት በሚል ፍቃድ የሚወስዱት ትክክለኛ አልሚዎች ሳይሆኑ ደላላዎች እንደነበሩ ገልጸው፥ እነዚህ ደላላዎች ለዓመታት ኢንቨስት የሚያደርግ ሰው ሲያፈላልጉ ስራ ሳይሰራ እንደሚቆይ አንስተዋል፡፡
በዚህ መንገድ ከሁለት ዓመታት በፊት ፈቃድ የወሰደው አካል መስራት ባለመቻሉ ከቻይና መንግስት ጋር በመነጋገር ጂሲጂ የሚባል የቻይና ኩባንያ ስራውን መረከቡንና በ14 ወራት ውስጥ ፕሮጀክቱን ማጠናቀቁን አንስተዋል።
የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዝ ማልማት እንደሚቻል የታየበት ሲሆን፥ በዚህም የሚቀጥለውን ዙር ለመጀመር በእጅጉ አግዟል ነው ያሉት።
በቅርቡ የተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የጋዝ ልማትና የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች በ24 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን የሚያስችልና በተለይም ሎጅስቲክስ ኢነርጂን ጨምሮ ለልማት ስራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በዋናነት ወጪ የምታወጣው ለነዳጅና ለአፈር ማዳበሪያ ሲሆን ይህንን በመተካት ከፍተኛ ሀብት መቆጠብ ትችላለች ብለዋል።
ጋዝ ለማዳበሪያና ለኢነርጂ ግብዓት እንደመሆኑ መጠን ለምግብ ዋጋ መጨመር አንዱ ምክንያት የሆነውን የትራንስፖርት ወጪ መቀነስ ከቻልን በከፍተኛ ደረጃ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ዳንጎቴ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚያለማው የማዳበሪያ ፋብሪካ 30 ሚሊየን ኩንታል ዩሪያ የሚያመርት ሲሆን፥ ከፋብሪካው በተጨማሪ ቨርቹዋል ላብራቶሪ፣ የፓኬጂንግ ስራ፣ትራንስፖርትና የምርት ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ቀጠና ውስጥ የሚሰሩት መሰረተ ልማቶች 10 ቢሊየን ዶላር ገደማ ሀብት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ የፋይናንስ ችግር ሳይገጥማቸው በታቀደላቸው ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ተናግረዋል።