ካልተደመርን በስተቀር የኢትዮጵያን ችግር ልንፈታ አንችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
ካልተደመርን በስተቀር የኢትዮጵያን ችግር ልንፈታ አንችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ካልተደመርን በስተቀር የኢትዮጵያን ችግር ልንፈታ አንችልም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ መሳሪያ ይዘው መንግስታትን ተቃርነው አሸንፈው ልማት እና ዴሞክራሲ ያመጣ የለም ብለዋል።
በመሳሪያ የሚመጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከመሳሪያ ያለፈ ነገር ማሰብ አይችሉም በማለት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ብቻ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
መንግስት ችግር አለብኝ ከሚል የትኛውም ኃይል ጋር ውይይት አድርጎ መፍትሄ ለማምጣት መስራቱን አንስተው፤ በአብነትም ከሸኔ እና ከትግራይ ወገኖች ጋር የተደረገውን ውይይት አመላክተዋል።
እኔን እና ጌታቸው ረዳን የተመለከተ ይህንን መንግስት አይወያይም ብሎ ማሰብ የሚያስገርም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሀገር ፍላጎት እስከተግባባን ድረስ የግሉን ጉዳዮቻችን ቸል ማለት አለብን ነው ያሉት።
ተላላኪዎች ታገልኩለት ለሚሉለት ህዝብ ማዳበሪያ እንዳይሄድ እያደረጉ፣ ልማት እያደናቀፉ፣ እየገደሉ ታገልኩልህ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ገልጸው፤ ነባር ችግሮችን በውይይት ህዝብ ሊወስንበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሁሉንም ያጠቃለለ ሀገራዊ ውይይት እንዲደረግ መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ገልጸው፤ በሆነ ዘመን ያለ ስርዓት በድሎናል ለሚሉ ደግሞ የሽግግር ፍትህ እናረጋግጥ፤ በይቅርታ ሊሆን በካሳ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት።
የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ መንግስት ለመወያየት በሩ ክፍት እንደሆነም ተናግረዋል።
አሁንም ለሰላማዊ ትግል በራችን ክፍት ነው፤ ካልተደመርን በስተቀር የኢትዮጵያን ችግር ልንፈታ አንችልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።