Fana: At a Speed of Life!

የከተማ አስተዳደሩ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የመዲናዋ ተማሪዎች የእውቅና መርሐ ግብር አከናውኗል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ከፖሊሲ ማሻሻል ጀምሮ የትምህርት ስርዓቱን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ500 በላይ ውጤት ካስመዘገቡ 1ሺህ 321 ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 336 ተማሪዎች እውቅና ሰጥተን አበረታተናል ብለዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመን ፈተናውን ከወሰዱት የመዲናዋ ተማሪዎች መካከል 21 ነጥብ 3 በመቶ ያህሉ ማለፋቸውን ያስታወሱት ከንቲባዋ፥ በ2017 ወደ 31 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም እንደ ሀገር ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ካሳለፉ 50 ትምህርት ቤቶች መካከል 17ቱ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙ ሁለት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ማሳለፍ መቻላቸው የስራችን ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል።

በተለይም ዛሬ የማበረታቻ ሽልማት ከሰጠናቸው መካከል ዐይነ ስውራንና መስማት የተሳናቸው ተማሪዎቻችን ለገጠማቸው የአካል ጉዳት ፈተና እጅ ሳይሰጡ ላስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት ትልቅ ክብር አለኝ ነው ያሉት።

የብልጽግና ዋነኛው መንገድ ትምህርት ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ የሚኖራቸው ቆይታ ለሀገር የሚጠቅም እውቀትና ክህሎት የሚቀስሙበት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች በተጨማሪ ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ትምህርት ቤቶችና ተቋማት እወቅና ተሰጥቷል፡፡

በቅድስት ብርሃኑ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.