ሀገር አቀፍ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይካሄዳል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይካሄዳል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፥ ምርጫ የአንድ ፓርቲ ሳይሆን የጋራ ፍላጎት መሆኑን አንስተዋል፡፡
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በፊት ከተደረጉት ምርጫዎች የበለጠ ግልፅና ተአማኒ እንደነበር አስታውሰው፥ መጪው 7ኛው ምርጫ ከዚህም የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሀሳብ ያለውና በምርጫው መሳተፍ የሚፈልግ ፓርቲ መሳተፍ እንደሚችል ገልጸው፥ ምርጫውን ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልፅና ተዓማኒ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እንደ መንግስትና ፓርቲ አማራጭ ድምፅ የሌለው ፓርላማ እንዲኖረን አንፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን በስራ ላይ ካለው ምክር ቤት በበለጠ ብዙ ድምፆች ይገባሉ የሚል ተስፋ አለኝ ነው ያሉት፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ምክክሩ ስርዓትን የሚያፈርስ ሳይሆን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰው፥ የመንግስት ስራዎች እየተከናወኑ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማምጣት መቋቋሙን አስረድተዋል፡፡
የሀገራዊ ምክከር ሂደቱ ከምርጫው በፊት የሚጠናቀቅ ከሆነ ለምርጫው ግብዓት የሚወሰድበት እንደሚሆን ገልጸው፥ ነገር ግን ምርጫውን የሚያስተጓጉል ነገር አይፈጠርም ነው ያሉት፡፡