ለቀይ ባሕር ጥያቄ የሚሰጠው አሉታዊ ምላሽ የኢትዮጵያ እድገት ለእኛ ስጋት ነው ከሚል ይመነጫል
ለቀይ ባሕር ጥያቄ የሚሰጠው አሉታዊ ምላሽ የኢትዮጵያ እድገት ለእኛ ስጋት ነው ከሚል ይመነጫል – የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባሉ አቶ ከማል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለቀይ ባሕር ጥያቄ ከኤርትራ በኩል የሚሰጠው አሉታዊ ምላሽ የኢትዮጵያ እድገት ለእኛ ስጋት ነው ከሚል ይመነጫል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከማል ሃሺ መሃሙድ፡፡
አቶ ከማል ሃሺ መሃሙድ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለጎረቤት ሀገራት ስጋት ሳይሆን በጋራ የማደግ ብስራት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡
ጉዳዩ ከለውጡ መንግስት የጎረቤት ሀገራት ግንኙነት ፖሊሲ አንጻር ሲታይ ቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነትን ብሎም ወንድማማችነትን ያጠናክራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪክ፣ ከሕጋዊነት፣ ከኢኮኖሚያዊ እና መልክዓ ምድራዊ ትስስር አንጻር ትክክልና ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም ጎረቤት ሀገራት ለባሕር በር ጥያቄው በሰጥቶ መቀበል መርሕ በጎ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ከባሕር በር ጋር በተያያዘ በኤርትራ በኩል የሚታየው ስጋት ጤናማ ካልሆነ ፉክክር እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ካለማክበር የሚመነጭ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቀይ ባሕር ለኤርትራ የተሰጠበት መንገድ ኢፍትሃዊነት ላይ ጥያቄ ሲነሳ ሁልጊዜም አስመራ መሰረተ ቢስ ውንጀላ እንደምታቀርብ ነው የገለጹት
በየትኛውም አመክንዮ ቀይ ባሕር የተወሰደበት መንገድ ትክልል አለመሆኑን ጠቅሰው ÷ ይህን ታሪካዊ ስህተት ማረም ተገቢ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ለባሕር በር ጥያቄው የሚሰጠው አሉታዊ ምላሽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመው ÷ ግድቡ ለጎረቤት ሀገራት ስጋት ሳይሆን የጋራ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ነው ብለዋል፡፡
ለባሕር ጥያቄ የሚሰጠው አሉታዊ ምላሽ የኢትዮጵያ እድገት ለእኛ ስጋት ነው ከሚል የተሳሳተ እና ግትር አቋም የተቀዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአሰብ ወደብ ለማንም በምንም መልኩ እዳይጠቅም መደረጉ ለዚህ ነው የሚሉት አቶ ከማል ÷ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የነበሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ለም/ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ÷ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ ነው ፤ማንም ፈለገም አልፈለገ ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ