የፋና ላምሮት ምዕራፍ 21 ውድድር በአዳዲስ ኮከቦች ቅዳሜ ይጀምራል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋና ላምሮት ምዕራፍ 21 ውድድር አዳዲስ ኮከቦችን ይዞ በመጪው ቅዳሜ ይጀምራል።
የምዕራፍ 21 ተወዳዳሪዎች ከ700 በላይ የቅድመ ማጣሪያ ተፎካካሪዎች መካከል የተለዩ 16 ከዋክብት ናቸው።
ውድድሩ ቅዳሜ ሲጀመር ስምንት ተወዳዳሪዎች ከኮከብ ባንድ ጋር ስራዎቻቸውን በሁለት ዙር ያቀርባሉ።
ለ13 ሳምንታት በሚዘልቀው በዚህ ምዕራፍ ተወዳዳሪዎች በተለያዩ ሳምንታት በራሳቸው፣ በዳኞች እና በተመልካቾች የሙዚቃ ምርጫ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።
የሙዚቃ ባለሙያዎች እና ተመልካቾች በአጭር የጽሑፍ መልዕክት በሚሰጡት ድምጽ ተወዳዳሪዎቹ የሚዳኙ ይሆናል።
በምዕራፉ ለፍፃሜ ለሚደርሱ አራት ተወዳዳሪዎች የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ለፋና ላምሮት 6ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በቀጥታ ያልፋሉ።
የምዕራፍ 21 ውድድር ቅዳሜ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ከ6:00 ጀምሮ በቀጥታ ስርጭት በፋና ቴሌቪዥን እና በፋና ዲጂታል ሁሉም አማራጮች ይተላለፋል።
በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት የተወዳዳሪዎችን ኮድ በመላክ እየተዝናኑ ድምጽ በመስጠት የዳኝነቱ አካል ይሁኑ።
በለምለም ዮሐንስ