ዩቬንቱስ – በተማሪዎች ተመስርቶ በስፖርቱ ዓለም የገነነ ስም
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከክርስቲያኖ ሮናልዶ እስከ ዚነዲን ዚዳን፣ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊ መሆን ከቻለው ሚሼል ፕላቲኒ እስከ አንድሪያ ፒርሎ እና ጂያንሉዊጂ ቡፎን በርካታ ከዋክብት የጣሊያኑን ገናና ክለብ ጥቁርና ነጭ ማልያ ለብሰው ተጫውተዋል፡፡
አሮጊቷ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የቱሪኑ ክለብ በጣሊያን ሴሪ አ 36 ዋንጫዎችን በማንሳት በ20 የስኩዴቶው ዋንጫዎች 2ኛ ላይ ከሚገኘው ኢንተር ሚላን በ16 ዋንጫ ልዩነት በከፍታ የተቀመጠ ኃያል ቡድን ነው፡፡
ከሀገር ውስጥ ውድድሮች ባለፈ 2 ጊዜ የሻምፒየንስ ሊግ፣ 3 ጊዜ የዩሮፓ ሊግ እንዲሁም 2 ጊዜ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ በማሸነፍ በአውሮፓ መድረክም በስኬታማነት ይታወቃል።
ይህ አንጋፋ ክለብ ዛሬ ላይ ስሙ በዓለም የናኘበት ስኬታማ ጉዞው የተጀመረው ከ128 ዓመታት ገደማ በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ነበር፡፡
መስራቾቹ ደግሞ በቱሪን ከተማ የሚገኘው ማሲሞ ዲ አዜግሊዮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ የቡድኑን መጠሪያ ‘ዩቬንቱስ’ ብለው የሰየሙት ‘ወጣት’ የሚለውን የላቲን ቃል በመጠቀም ነው።
አሮጊቷ በሚለው ቅጽል ስም በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ዩቬንቱስ በተመሰረተ በ3ኛ ዓመቱ ነበር በያኔው አጠራሩ የጣሊያን እግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ በመባል በሚታወቀው የጣሊያን ሴሪ አ መሳተፍ የጀመረው፡፡
ከአምስት ዓመታት የውድድሩ ተሳትፎ በኋላ አንድ ብሎ የጀመረውን የሊጉ ዋንጫ ስኬት አሁን ላይ 36 በማድረስ የሚተካከለው ቡድን የለም፡፡
ከ36ቱ የስኩዴቶው ዋንጫዎች ውስጥ ዘጠኙን ከ2011 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት በተከታታይነት የግሉ አድርጓል።
ከእነዚህ ዘጠኝ ተከታታይ ዋንጫዎች ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዋንጫዎች በአንቶኒዮ ኮንቴ፣ አምስቱን በማሲሚላኖ አሌግሪ እንዲሁም ቀሪዋንና የመጨረሻዋን ዋንጫ በማውሪዚዮ ሳሪ እየተመሩ ነበር ማሸነፍ የቻሉት፡፡
የተለያዩ ተጫዋቾች ለዩቬንቱስ እየተጫወቱ በነበረበት ወቅት ስምንት ጊዜ ባሎንዶርን ያሸነፉ ሲሆን፥ በዚህም ከሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ቀጥሎ 3ኛው ክለብ ነው፡፡
ሚሼል ፕላቲኒ የክለቡ ተጫዋች በነበረበት ወቅት ለተከታታይ ሦስት ጊዜ ይህንን ማሳካት የቻለ ሲሆን፥ ዚነዲን ዚዳን፣ ሮቤርቶ ባጂዮ፣ ፓውሎ ሮሲ፣ ፓቬል ኔድቬድ እና ኦማር ሲቮሪ በቱሪን ቆይታቸው እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ይህንን ክብር ተቀዳጅተዋል፡፡
ምንም እንኳ በቱሪን ቆይታቸው የባሎንዶር ተሸላሚ ባይሆኑም ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ፋቢዮ ካናቫሮ፣ አንድሪያ ፒርሎ፣ ዴል ፔሮ እና ጂያንሉዊጂ ቡፎን ጥቁር እና ነጩን ማልያ ለብሰው ከተጫወቱ ስመ ጥር ተጫዋቾች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ዩቬንቲኒ በመባል የሚታወቁትና የአሊያንዝ ስታዲየም ድምቀት የሆኑት የክለቡ ደጋፊዎች “ፊኖ አላ ፊኔ ፎርዛ ዩቬንቱስ” በሚለው ኅብረ ዝማሬያቸው ለክለባቸው እስከመጨረሻው የመፋለም ጉልበት ሆነው ዓመታትን ዘልቀዋል።
በተለይም በፈረንጆቹ 2006 ከዳኞች ጋር በመመሳጠር በተፈጸመ የእግር ኳስ የሙስና ቅሌት ዩቬንቱስ ወደ ታችኛው ሊግ እንዲወርድ ሲገደድ ስታዲየሙን በመሙላት ለክለባቸው ታማኝነታቸውን አሳይተዋል።
ከጣሊያን ባሻገር በዓለም የናኘ ስም ባለቤት የሆነው ዩቬንቱስ ለመጨረሻ ጊዜ የስኩዴቶው ባለክብር ከሆነበት 2019/20 ወዲህ ከሊጉ ዋንጫ ጋር ተራርቆ ቆይቷል፡፡
የመጨረሻውን ዋንጫ ያሳኩትን ማውሪዚዮ ሳሪ ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ክለቡን የመሩት አምስት አሰልጣኞች ክለቡን ወደለመደው ስኬት ለመመለስ ተቸግረዋል፡፡
የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም የናፖሊ፣ ኢንተር ሚላን፣ ሮማ የቀድሞ አሰልጣኝ ሉቺያኖ ስፓሌቲ ባሳለፍነው ሰኞ የተሰናበቱትን ኢጎር ቱዶር ተክተው የዩቬንቱስ አሰልጣኝ በመሆን ተሹመዋል።
የ66 ዓመቱ ጣሊያናዊ የቱሪኑን ክለብ ወደ ቀደመው ኃያልነት የመመለስ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ