የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤን በመለወጥ የተሟላ ብልጽግና ማረጋገጥን ያለመ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማን ለመገንባት የኮሪደር ልማቱን ከአዲስ አበባ በመጀመር ሁሉም ክልሎች ላይ ከተሞችን የማልማት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህ የኮሪደር ልማት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ከማረጋገጥ አኳያ የጎላ ሚና አለው፡፡
አዲስ አበባ ከኮሪደር ልማት በፊት ምን እንደምትመስል ልማቱ ሲጀመር የነበረውን ሁኔታና የኮሪደር ልማቱ ካለቀ በኋላ ያለውን ለውጥ የሚያሳይ ልምድ በመውሰድ በመላው ኢትዮጵያ 68 ከተሞች ላይ የኮሪደር ልማት መስራት ተችሏል፡፡
የኮሪደር ልማት ከከተሜነት ዕድገት ጋር የተሳሳረ ልማት ሲሆን፥ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ልማት ለዜጎቻችን ለማቅረብ በማለም ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ ሊሆን በሚችል መልኩ ከተሞች እያለሙ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው ገጠር በመሆኑ የዜጎችን ህይወት ለመቀየርና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በከተማ የተሰራ የኮሪደር ልማት በቂ አይደለም፡፡ በከተሞች የታየው አመርቂ ውጤት በገጠርም መታየት አለበት፡፡
ስለዚህ የኮሪደር ልማቱ በከተማ ብቻ ሳይገደብ የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2017 ግንቦት ወር መጨረሻ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን ሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በመቀነስ የተመጣጠነ ዕድገትን ለማምጣት የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡
ይህ ደግሞ የተስተካከለ ኑሮንና ከተሜነትን ወደ ገጠር በማምጣት፣ ሞዴል የገጠር መንደሮች ቀላል ወጪ የሚጠይቁና በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ እንዲሁም አርሶ አደሩ ጤናማና ክብር ያለውን ህይወት እንዲኖር የሚያስችል የልማት አካል ነዉ።
የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ስነ ምህዳራዊ ፋይዳን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ሲሆን፥ ይህም ዘላቂ ልማትና የተረጋጋ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ከለውጡ በፊት የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነው የገጠሩ አካባቢ ትኩረት ተነፍጎት የቆየ ሲሆን፥ የለውጡ መንግሥት የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ከተማ የሚሄደውን አርሶ አደር በሚኖርበት ተረጋግቶ እሴት መጨመር ላይ እየሰራ እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል።
የገጠር ኮሪደር አጠቃላይ የኅብረተሰብ ሽግግርን የሚያመጣና መሰረተ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮችን ያቀፈ ሲሆን፥ በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ አኗኗርን የሚፈጥርና የአርሶ አደሩን ህይወት የሚቀይር ይሆናል።
በአጠቃላይ የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ዘመናዊ ስልተ ምርት እንዲከተል የሚያደርግ ሲሆን፥ አርሶ አደሩ ባህሉን እና ወጉን ጠብቆ አካባቢውን ንጹህ፣ ጓሮውን በዶሮ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በማርና ወተት ምርት የተትረፈረፈ በማድረግ ቀላል የአኗኗር ስልት እንዲከተል ያደርጋል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት