Fana: At a Speed of Life!

ከአስከፊ የጎዳና ሕይወት ሕልምን ወደማሳካት…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኤልናታን ሞናናው ገና በሰባት ዓመት ዕድሜው ነበር የቤታቸው ምሶሶ የሆኑት አባቱን በሞት የተነጠቀው፡፡

የአባቱን ሕልፈት ተከትሎም የክፉ ቀን መጠጊያ ይሆናሉ ያላቸው ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ ፊታቸውን አዞሩበት፡፡

በዚህ ምክንያትም ገና በለጋ ዕድሜው ወደ ጎዳና በመውጣት አስከፊውን የኑሮ ተራራ መግፋት ዕጣው ሆነ።

ኤልናታን ችግር እንደ አየር በዙሪያ በሚነፍስበት፣ ረሃብ እና ነፋስ ጎረቤት በሆኑበት፣ ብቸኝነት ብቻ ዘመድ በሆነበት የጎዳና ሕይወት ውስጥ ተስፋ የሚባል አንዳች ነገር አላገኘም።

ይልቁንም በዚህ የጎዳና ሕይወት ውስጥ ከከበበው በርካታ ችግር ለመደበቅ፣ ለመርሳት እና ነገሮችን ላለማስታወስ የተለያዩ ሱሶች ውስጥ መግባቱን ይናገራል፡፡

የጎዳና ሕይወት አስከፊ ገጽታ ብዙ ነው የሚለው ባለታሪኩ÷ ሁኔታው በንግግር ብቻ ተነግሮ የሚገለጽ እንዳልሆነና ብዙ አስፈላጊ ነገሮችን በማጣቱ ከፍተኛ የሆነ የስሜት ጉዳት እንደደረሰበት ያስረዳል፡፡

በዚሁ የጎዳና ሕይወት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም አካባቢ እና በመገናኛ አካባቢ ከተለያዩ በጎዳና ሕይወትን ከሚመሩ ጓደኞቹ ጋር ከባድ የሆኑ ዓመታትን እንዳሳለፈ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግሯል፡፡

ነገር ግን ኤልናታን በወቅቱ እንደ አረንቋ የከበበው የጨለማ ሕይወት ከርቀት ያለውን ብሩህ ተስፋ እንዳይመለከት አላገደውም።

በዚህም በጎዳና ሕይወት ውስጥ በሚገጥሙት አስከፊ ሁነቶች ሳይበገር በምስቅልቅል ውስጥ ሆኖ ትምህርቱን በመቀጠል ወደ ተመለከተው ብሩህ ተስፋው መገስገስ ይጀምራል።

ወጣት ኤልናታን ምሳ ተቋጥሮ እና ልብሳቸው ታጥቦ ወደ ት/ቤት ከሚመጡ ተማሪዎች ጋር ተቀምጦ ከትምህርት ቤቱ ክበብ የሚቀበለውን ትርፍራፊ ምግብ እየተመገበ ትምህርቱን ይከታተል ነበር።

በትምህርት ቤት ውስጥ ስለእኔ አኗኗር እና ማንነት ሲወራ እንዳልሰበር ራሴን አጽናና ነበር የሚለው ኤልናታን፥ ስለእርሱ የሚያውቁ እና የሚያበረታቱ ጓደኞች እንደነበሩትም ያስታውሳል።

በዚህ ዓይነት የሕይወት ጉዞ መልካም እና መጥፎ የሕይወት ክስተቶችን እንደየ አመጣጣቸው ተቀብሎ በማስተናገድ ሕይወቱን በሚቀጥልበት ወቅትም በጎ ልብ ባለው አንድ ጀርመናዊ ዜጋ ከጎዳና ሕይወት መውጣት መቻሉን ይናገራል፡፡

በትምህርቱ ገፍቶ ዩኒቨርሲቲ በመማርም የመጀመሪያ ዲግሪውን ያጠናቀቀ ሲሆን÷ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በተለያዩ ኃላፊነቶች በማገልገል ላይ ይገኛል። ትዳር በመመስረትም የሁለት ልጆች አባላት ለመሆን በቅቷል።

በጎዳና ሕይወት ውስጥ አብሮት ያሳለፈው ፒተር ቸሩ ስለ ኤልናታን ሲናገር÷ በጎዳና ላይ ከሚኖሩ ልጆች የተለየ ጸባይ እንዳለው እና ከልጅነቱ ጀምሮ በርካቶችን የመርዳት ሕልም እንደነበረው ያስታውሳል።

የችግርን አስከፊነት እስከ ጥግ ድረስ ወርዶ የተመለከተው ይህ ወጣት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ በነበረበት ወቅት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምን በፈተነበት ጊዜ በጎዳና የሚኖሩ እና አቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ የበጎ አድራጎት ሥራውን አሃዱ ብሎ መጀመሩን ያስረዳል፡፡

ያኔ በለጋ ዕድሜው አንዲት ጉርሻ ለማግኘት ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍል እንደነበረ በማውሳት፥ በጎዳና ላይ የሚገኙ ወገኖች ጋር በመሄድ የሕይወት ተሞክሮውን በማጋራት ተስፋ የመስጠት እና የምገባ እንዲሁም የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን ያስታውሳል።

ይህንን በማድረጌ የበለጠ እንድነሳሳ አድርጎኛል የሚለው ባለታሪኩ ከኮቪድ በኋላም በየአካባቢው ያሉ ባለሃብቶችን በማስተባበር አጋዥ የሌላቸውን ወገኖች ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረጉን ይገልጻል።

ትናንት ላይ ደግ ልብ ያላቸው ሰዎች ከጎዳና ሕይወት እንድወጣ ባያግዙኝ ኖሮ ዛሬ እዚህ ደረጃ መድረስ አልችልም ነበር የሚለው ኤልናታን÷ በኢትዮጵያውያን የመተባበር ባህል ስንደጋገፍ ምንም ነገር ማሳካት እንችላልን ሲል አጽንዖት ሰጥቷል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.