ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጄሬሚ ሮቤር ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ ከሚገኘው የኢትዮጵያ እና አውሮፓ የኢንቨስትመንት ፎረም ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሰጡት መመሪያ መሰረት የኢንቨስትመንት ፎረሙ መካሄዱ ትልቅ ስኬት መሆኑን አማካሪው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት በቀጣናው ስላሉ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታዎች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በፎረሙ የነበራቸው ተሳትፎ የሚያበረታታና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚያግዝ የተገለጸ ሲሆን፥ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያና ለበርካታ ፕሮጀክቶች ስታደርገው የነበረውን ድጋፍ እንደምትቀጥል በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ይበልጥ በማጠናከር ትስስራቸውን ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደርሷል::