Fana: At a Speed of Life!

ዝምተኛው የእግር ኳስ ጥበበኛ ቶኒ ክሩስ…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አቻ በሌለው እይታው እና መስመር ሰንጣቂ ኳሶቹ ይታወቃል ጀርመናዊ የእግር ኳስ ጥበበኛ ቶኒ ክሩስ፡፡

በፈረንጆቹ 1990 በምስራቅ ጀርመን ግሪፍስዋልድ የተወለደው ቶኒ ክሩስ÷ የእግር ኳስ ሕይወቱን ጅማሮ ያደረገው በአካባቢው በሚገኝ ግሪፍስዋልደር በተሰኘ ክለብ ነው፡፡

በ2007 በ17 ዓመቱ ለባየርን ሙኒክ ዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨወታውን ያደረገው ክሩስ ለ18 ወራት ለባየርሊቨርኩሰን በውሰት ተጫውቷል፡፡

በ2010 ዳግም ወደ እናት ክለቡ ባየርን የተመለሰው ክሩስ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች በመሆን ሶስት የቡንደስሊጋ፣ አንድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁም ሁለት የዲኤፍቢ ፖካል ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል፡፡

በተጨማሪም ሶስት ጊዜ የቡንደስሊጋው የዓመቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ መቀላቀል የቻለው ዝምተኛው አማካይ በ2014 ለስፔኑ ሃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ በ25 ሚሊየን ዩሮ ፊርማውን አኑሯል፡፡

በሪያል ማድሪድ ቆይታው 306 ጨዋታዎችን ማደረግ የቻለው ቶኒ ክሩስ 22 ግቦችን ለክለቡ አስቆጥሯል፡፡

ክሩስ በ2024 ጫማውን እስከሰቀለበት ጊዜ ድረስ በሪያል ማድሪድ ባሳለፋቸው ዓመታት አራት የላሊጋና አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ዋንጫዎችን አሸንፏል፡፡

በሎስብላንኮሶቹ ቆይታው ሪያል ማድሪድ ከ2016 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት በተከታታይ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ሲያሸንፍ ቶኒ ክሩስ በሶስቱም ዓመታት የውድድሩ የዓመቱ ምርጥ ቡድን ስብስብ ውስጥ መካታት ችሏል፡፡

እንዲሁም የላሊጋ ምርጥ ቡድን ስብስብ ውስጥ ሁለት ጊዜ፣ የፊፋ የዓለም ምርጥ 11 ውስጥ አራት ጊዜ የተካተተው አማካዩ ÷ በ2018 እና 2024 የጀርመን የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል፡፡

በዋናው ብሄራዊ ቡድን በ2010 በ20 ዓመቱ ጥሪ የተደረገለት ቶኒ ክሩስ ለሀገሩ 114 ጨዋታዎችን በማድረግ 17 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡

በ2014 ጀርመን የዓለም ዋንጫን ስታሸንፍ የክሩስ ሚና ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ÷ በውድድሩ ከፍተኛው ለግብ የሆኑ ኳሶችን ያቀበለ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡

አቻ በሌለው መስመር ሰንጣቂ ኳሶቹ እና እይታው የሚታወቀው ዝምተኛው ጥበበኛ ቶኒ ክሩስ ከምንጊዜም ታላላቅ አማካይ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡

በ17 ዓመታት የእግር ኳስ ተጫዋችነት ጉዞው 34 ዋንጫዎችን ባሳለፈባቸው ክለቦች እንዲሁም ከሀገሩ ጋር ማንሳት የቻለው ክሩስ ከቶማስ ሙለር (35) በመቀጠል በበርካታ ዋንጫዎች የተንበሸበሸ ጀርመናዊ ተጫዋች ነው፡፡

የ35 ዓመቱ ቶኒ ክሩስ ከበርከታ ስኬቶቹና ትዝታዎቹ ጋር ዓመታትን ከኖረበት እግር ኳስ መለያየቱን በፈረንጆቹ 2024 ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በአቤል ነዋይ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.