Fana: At a Speed of Life!

በውድድር ዓመቱ 16ቱንም ጨዋታዎች ያሸነፈው ባየርን ሙኒክ…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጀርመኑ ክለብ ባየርን ሙኒክ በዚህ የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድር ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ባየርን ሙኒክ በውድድር ዓመቱ በሁሉም ውድድሮች ያደረጋቸውን 16 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በማድረግ ያለመሸነፍ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በአሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ የሚመራው ባየርን ሙኒክ በ16 ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቹ ላይ 56 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን÷ የተቆጠረበት 11 ግብ ብቻ ነው፡፡

በ2023/24 የውድድር ዓመት የቡንደስሊጋውን ክብር በባየር ሊቨርኩሰን የተነጠቀው ሙኒክ÷ በ2024/25 በአሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ አማካኝነት ወደለመደው ክብሩ መመለሱ ይታወሳል፡፡

በፈረንጆቹ 2024/25 የውድድር ዘመን ባየርን ሙኒክን የተረከበው ቤልጄማዊው አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የቡንደስሊጋውን ዋንጫ ለማሳካት የሚያደርገውን ጉዞ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ በርንሌይን ወደ ሊጉ ቢያሳድግም በሊጉ ማቆየት እንዳልቻለ የሚታወስ ሲሆን÷ በሙኒክ ግን ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡

በዚህ ሳምንት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ወደ ፈረንሳይ አቅንቶ የአምና የመድረኩ አሸናፊ ፒኤስጂን ያሸነፈው ሙኒክ÷ በ2025/26 የውድድር ዘመን በሻምፒየንስ ሊጉ ሁሉንም ጨዋታዎች ካሸነፉ ሦስት ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡

ለባየርን ሙኒክ የውጤት ማማር ትልቁን ድርሻ ከሚወስዱ ተጫዋቾች መካከል ሃሪ ኬን፣ ሉዊስ ዲያዝ እና ኦሊሴ የመሳሰሉ ተጫዋቾች ይጠቀሳሉ፡፡

እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ሃሪ ኬን በዚህ የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች ለሙኒክ 22 ግቦችን አስቆጥሮ 3 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

በ12 ግቦች የቡንደስሊጋውን ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃ የሚመራው ሀሪ ኬን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ 5 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን÷ በሻምፒየንስ ሊጉ የሚበለጠው በቪክቶር ኦሲሜን ብቻ ነው፡፡

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሙኒክን የተቀላቀለው ሉዊስ ዲያዝ ሌላኛው የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ኮሎምቢያዊው የፊት መስመር ተጫዋች ዲያዝ በሁሉም ውድድር 10 ግቦችን አስቆጥሮ 5 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

ከቡድኑ ጥንካሬዎች ውስጥ የሚጠቀሰው ኦሊሴ በውድድር ዓመቱ 14 ግቦች ላይ በቀጥታ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡

የ39 ዓመቱ አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ ከቡድኑ ወቅታዊ ብቃት ጋር ተያይዞ ለተጫዋቾቹ ባስተላለፈው መልዕክት አድናቆት ሲመጣ አትመኑ ያን ያህል ጥሩ አይደለም ሲል ተደምጧል፡፡

ቤልጄማዊው አሰልጣኝ እስከ ፈረንጆቹ 2029 ድረስ በባየርን ሙኒክ ለመቆየት በቅርቡ ውሉን ማራዘሙ ይታወሳል፡፡

እስካሁን 16 ጨዋታዎችን በተከታታይ ብናሸንፍም ቀጣዩን ጨዋታ ለማሸነፍ ጠንክረን መስራት አለብን በማለት ለተጫዋቾቹ ተናግሯል፡፡

ነገ በ10ኛ ሳምንት የጀርመን ቡንደስሊጋ መርሐ ግብር ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ኡኒየን በርሊንን የሚገጥመው ሙኒክ ያለመሸነፍ ጉዞውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

በተከታታይ 16 ጨዋታዎችን ድል ያደረገው የአሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ ባየርን ሙኒክ የተከታታይ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ እስከ ምን ድረስ ይሄዳል የሚለው ይጠበቃል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.