የጋርዲዮላ አዲስ ምዕራፍ – ማንቼስተር ሲቲ ከሊቨርፑል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማንቼስተር ሲቲ ከሊቨርፑል፣ ቶተንሃም ከማንቼስተር ዩናይትድ እንዲሁም ሰንደርላንድ ከአርሰናል የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ የ11ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ከ30 ቶተንሃም ሆትስፐር ማንቼስተር ዩናይትድን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጀምራል፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ ከቶተንሃም ጋር ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፎ፥ ሁለቱን አቻ የተለያየ ሲሆን ማሸነፍ አልቻለም፡፡
በሌላ የዛሬ ተጠባቂ መርሐ ግብር በሁሉም ውድድሮች ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያልተቆጠረበት የሊጉ መሪ አርሰናል ወደ ስታዲየም ኦፍ ላይት አቅንቶ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘውን ሰንደርላንድ ይገጥማል፡፡
ስዊዘርላንዳዊው የቀድሞ መድፈኛ ግራኒት ዣካ የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒ በሚገጥምበት የምሽቱ ጨዋታ የሰሜን ለንደኑ ክለብ መሪነቱን ለማጠናከር ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
ቼልሲ አሰልጣኝ ጋሪ ኦኔልን ያሰናበተውን ዎልቭስን ምሽት 5 ሰዓት ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ያስተናግዳል፡፡
በሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች ኤቨርተን ከፉልሃም እንዲሁም ዌስትሃም ከበርንሌይ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ይገናኛሉ፡፡
ፕሪሚየር ሊጉ ነገ ሲቀጥል፥ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ማንቼስተር ሲቲ ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ሲቲን እየመሩ ሊቨርፑልን በሚገጥሙበት የነገ ምሽቱ ጨዋታ 1 ሺህ እና ከዚያ በላይ ጨዋታዎችን መምራት ከቻሉ አሰልጣኞች ተርታ ስማቸውን ማስፈር ይችላሉ፡፡
በዘመናዊ እግር ኳስ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ አሰልጣኞች አንዱ የሆኑት ስፓኒያርዱ አሰልጣኝ በባርሴሎና ዋናውና 2ኛው ቡድን እንዲሁም በባየርን ሙኒክ እና ማንቼስተር ሲቲ በአሰልጣኝነት በመሯቸው 999 ጨዋታዎች 715 ያህሉን በድል ተወጥተዋል።
አሰልጣኝነትን ሲጀምሩ አንድም ቀን 1 ሺህ ጨዋታዎችን እመራለሁ የሚል ግምት ያልነበራቸው ፔፕ፥ ይህ ስኬት የተለየ ትርጉም አለው ብለዋል።
ማንቼስተር ሲቲዎች ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አራቱን አሸንፈው በአንዱ ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን፥ ሊቨርፑል በአንጻሩ ባለፈው ሳምንት አስቶን ቪላን በመርታት በሊጉ ከአራት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ እርስ በርስ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሁለቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡
ማንቼስተር ሲቲ በአንዱ ጨዋታ ድል ሲቀናው በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
በሌሎች የነገ ጨዋታዎች ብሬንትፎርድ ከኒውካስል፣ አስቶን ቪላ ከቦርንማውዝ፣ ክሪስታል ፓላስ ከብራይተን እንዲሁም ኖቲንግሃም ፎረስት ከሊድስ ዩናይትድ በተመሳሳይ 11 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን አርሰናል ከተከታዩ ማንቼስተር ሲቲ በስድስት ነጥብ ርቆ በ25 ነጥብ እየመራ ይገኛል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ