Fana: At a Speed of Life!

ድርቅን የሚቋቋሙና የተሻለ ምርት የሚያስገኙ ሀገር በቀል የስንዴ ዝርያዎች…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ድርቅን የሚቋቋሙና የተሻለ ምርት ያስገኛሉ ተብለው የተለዩ ሀገር በቀል የስንዴ ዝርያዎችን ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት፡፡

በኢንስቲትዩቱ የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ ውብሸት ተሾመ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ ከ80 ያህል የስንዴ ዝርያዎች ውስጥ ድርቅን የሚቋቋሙና የተሻለ ምርት የሚያስገኙ አራት ሀገር በቀል የስንዴ ዝርያዎች ተለይተዋል፡፡

ሀገር በቀል የስንዴ ዝርያዎቹ ኢንስቲትዩቱ ባቋቋማቸው የዘር ባንኮች አማካኝነት የአርሶ አደሮችን ነባር እውቀት በመጠቀም በማሳ ላይ ተሞክረው ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የተለዩት ዝርያዎች የስንዴ ምርጥ ዘር ከሚጠቀመው የአፈር ማዳበሪያ ሩብ ያህሉን ብቻ በመጠቀም በሔክታር እስከ 58 ኩንታል ምርት ይገኝባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ሀገር በቀል የስንዴ ዝርያዎቹ ከምርታማነታቸው በተጨማሪ ድርቅንና የዋግ በሽታን መቋቋም የሚችሉ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ሌሎች የስንዴ ዝርያዎች ምርት መስጠት ባልቻሉበት የድርቅ ወቅት፥ የተለዩት ዝርያዎች ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ተዘርተው በሔክታር እስከ 15 ኩንታል ምርት እንደተገኘባቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በሚኖርበት ወቅት ርጥበትን ተቋቁመው ምርት የሚያስገኙ ሀገር በቀል የስንዴ ዝርያዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

እነዚህን የተሻሻሉ ሀገር በቀል የስንዴ ዝርያዎች በማባዛት ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት እንዲቻል ያላቸውን ባህሪያት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ውብሸት የገለጹት፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.