Fana: At a Speed of Life!

ቢቢሲ የትራምፕን ንግግር ቆርጦ በመቀጠል ያሰራጨው መረጃና መዘዙ…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቢቢሲ ከዋና ፕሮግራሞቹ መካከል አንዱ በሆነው ፓኖራማ ላይ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር ዙሪያ ስለተሰራ ዘጋቢ ፊልም አዲስ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ከፍተኛ ትችት እያስተናገደ ሲሆን የተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊዎችም ሥራቸውን ለቀዋል፡፡

ጉዳዩ የጀመረው ዘ ቴሌግራፍ የቀድሞ የቢቢሲ የውጭ አማካሪ ሚካኤል ፕሬስኮትን ደብዳቤ ዋቢ በማድረግ በኮርፖሬሽኑ ውስጥ “ከባድ እና ሥርዓታዊ” አድልዎ ብሎ የጠራውን ጉዳይ ማጋለጡን ተከትሎ ነው።

በ2024 “ትራምፕ ሁለተኛ ዕድል?” በሚል ርዕስ በተሰራጨው ዘጋቢ ፊልም ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ 2021 ያደረጉትን ንግግር ቆርጦ በመቀጠል የካፒቶል ጥቃት እንዲፈጸም ያበረታቱ እንዲመስል ተደረጎ የተሰራ ነው።

ቢቢሲ በፕሮግራሙ ላይ ትራምፕ በአንድ ሰዓት ልዩነት ውስጥ የተናገሯቸውን ሁለት የተለያዩ ሃሳቦች በመገጣጠም የ2021ን የካፒቶል ሂል አመጽ እንደደገፉ አድርጎ ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡

ቢቢሲ ትራምፕ “ወደ ካፒቶል እንሄዳለን እኔም ከእናንተ ጋር እሆናለሁ፣ ጀግኖች ሴናተሮች እና የኮንግረስ አባላትን እናበረታታለን” የሚለውን ሐረግ ከተናገሩ ከ45 ደቂቃዎች በኋላ የተናገሩትን “በርትተን እንዋጋለን” የሚለውን ሐረግ ቆርጦ በመቀጠል “ወደ ካፒቶል እንሄዳለን… እንዋጋለን” እንዳሉ አድርጎ አስመስሏቸዋል።

እንዲሁም ዘጋቢ ፊልሙ ትራምፕ ደጋፊዎቹ “በሰላማዊና በአርበኝነት ስሜት እንዲሰለፉ” የሰጡትን ጥሪም ቆርጦ ያወጣው ሲሆን ÷ ንግግሩን ከመጀመሩ በፊት የተቀረጸውን ደጋፊዎቹ ወደ ካፒቶል ሲሄዱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መጨረሻ ላይ በመጠቀም ለቅስቀሳው ምላሽ እንደሰጡ አድርጎ ያስመለክታል።

የቢቢሲ አማካሪው ፕሬስኮት በወቅቱ ባቀረበው ሪፖርቱ ላይ እንዲህ ዓይነቱ ስራ የቢቢሲን ትክክለኛነትና ፍትሃዊነት ደረጃን እንደሚጥስ እና ትራምፕ በእርግጥ ያልተናገሯቸውን ነገሮች እንዲናገሩ አድርጓል በማለት ማስጠንቀቂያ ቢያቀርብም የቢቢሲ ሥራ አስፈጻሚዎች ውድቅ አድርገውበት ነበር።

አሁን ላይ ታዲያ ዘ ቴሌግራፍ የፕሬስኮትን ሪፖርት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ተቃውሞው እየጨመረ የመጣ ሲሆን÷ የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር እና የዜና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል።

የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ በቅርቡ የተከሰቱ ውዝግቦችና ስህተቶች ለስራ መልቀቃቸው አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አንስተው ቢቢሲ ሁልጊዜም ክፍት፣ ግልጽ እና ተጠያቂ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

የዜና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዴብራ ተርነስ በበኩላቸው÷ በትራምፕ ዘጋቢ ፊልም ላይ ያለው ውዝግብ ቢቢሲ ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ በመግለጽ ኃላፊነታቸውን ለቀዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ÷ ዘ ቴሌግራፍ ሙሰኛ ጋዜጠኞችን ስላጋለጠ አመስግነው እነዚህ ሐቀኛ ያልሆኑ ሰዎች በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሚዛን ላይ ለመራመድ የሞከሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ድርጊቱ ለዴሞክራሲ አስከፊ ነገር መሆኑን ያስገነዘቡት ፕሬዚዳንቱ ÷ ቢቢሲ ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ የባህል፣ ሚዲያ እና ስፖርት ኮሚቴ ቢቢሲ ለፕሬስኮት ክሶች ምላሽ እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን ÷ ከተለያዩ ፓርቲዎች የተውጣጡ የፖለቲካ መሪዎች ቢቢሲ ላይ ከታች እስከ ላይ ድረስ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.