በሁለት ዓመት ውስጥ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የሥራ ገበያ የሁለትዮሽ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ በሁለት አመት ውስጥ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል አለ በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፡፡
ኢትዮጵያ በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ እየተካሄደ በሚገኘው 7ኛው የሰው ኃይልና ማህበራዊ ልማት ኤክስፖ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡
በሳኡዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምሳዳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) በኤክስፖው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፥ ሁለቱ ሀገራት ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነታቸውንና መልክዓ ምድራዊ ቅርበታቸውን በመጠቅም ለሁለንትናዊ ዕድገት በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።
የሁለቱን ሀገራት የእድገት ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሽጋገር በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂና በእውቀት ሽግግር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በፈረንጆቹ 2023 በሥራ ገበያ ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት፡፡
ህጋዊ ማዕቀፍ ተበጅቶለት የተጀመረው የውጭ ሥራ ስምሪት ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ለጋራ ብልፅግና የላቀ አስተዋፅኦ ማበርከት መጀመሩን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በኤክስፖው ላይ መሳተፏ በሰው ኃይልና አቅርቦት ገበያ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተወዳዳሪ ሆና ለመቀጠል፣ የስራ እድልን ለማመቻቸት፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቀነስ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት መልካም እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በኤክስፖው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ሀገራት እየተሳተፉ ሲሆን፥ በሰው ኃይል ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን ለማገናኘት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።