በፈርጉሰን የሚወደደው ፖል ስኮልስ…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት የራሱን ትልቅ አሻራ ያስቀመጠና በሰር አሌክስ ፈርጉሰን የሚወደድ ተጫዋች ነው ፖል ስኮልስ፡፡
እንግሊዛዊው የቀድሞ የማንቼስተር ዩናይትድ ተጫዋች ፖል ስኮልስ በእግር ኳስ ሕይወቱ ከቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር ስኬታማ ጊዜ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና በእግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ምርጥ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ስኮልስ÷ በቀድሞ የማንቼስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ተወዳጅ እንደነበር አይዘነጋም።
ፖል ስኮልስ 11 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን በማሳካት ከእንግሊዛዊያን ተጫዋቾች ሁሉ ቀዳሚ ነው።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ በእግር ኳስ ሕይወቱ በአጠቃላይ 25 ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
ሰኮልስ በክህሎቱ፣ ኳስ በማቀበል ብልሃቱ እና ከርቀት በመምታት ግብ በማስቆጠር ብቃቱ ሁሌም የሚታወስ ተጫዋች ነው።
ፖል ስኮልስ 718 ጨዋታዎችን ለማንቼስተር ዩናይትድ በማድረግ በክለቡ ታሪክ ከሪያን ጊግስ፣ ጀምስ ሃሪሰን እና ቦቢ ቻርልተን በመቀጠል በርካታ ጨዋታዎችን ያደረገ 4ኛው ተጫዋች ነው።
በፈረንጆቹ 2011 ራሱን ከእግር ኳሱ ዓለም ማግለሉን ቢያሳውቅም ጫማውን ከሰቀለበት በማውረድ በፈረንጆቹ 2012 እንደገና ወደ ሜዳ በመመለስ መጫወቱ ይታወሳል።
ስኮልስ ጫማውን ከሰቀለበት በማውረድ ለአንድ የውድድር ዘመን ከተጫወተ በኋላ በፈረንጆቹ 2013 በድጋሚ ወደ ሜዳ ላይመለስ ራሱን ከእግር ኳሱ ዓለም አግልሏል።
ፖል ስኮልስ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን 66 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን÷ በ1998 እና 2002 የዓለም ዋንጫ እንዲሁም በ2000 እና 2004 የአውሮፓ ዋንጫ ሀገሩን ወክሏል።
በ1998/99 የውድድር ዘመን ማንቼስተር ዩናይትድ የሶስትዮሽ ክብር ባለቤት ሲሆን÷ ስኮልስ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነበር።
በፈረንጆቹ 2004 የቀድሞ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሶቅራጥስ ስለ ስኮልስ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ስኮልስን ሲጫወት ማየት ያስደስተኛል በማለት ተናግሮ ነበር።
የቀድሞ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ዚነዲን ዚዳን በበኩሉ÷ ስኮልስ ያለ ጥርጥር የትውልዱ ታላቅ አማካኝ ነው ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
ሮናልዲኒሆ ጎቹ፣ ሉዊስ ፊጎ፣ አንድሬስ ኢኔሽታ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ዋይን ሩኒ እና አለን ሽረር የስኮልስ ልዩ የእግር ኳስ ተሰጥኦ አድናቂ ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ስኮልስ ኳሱን ከመቀበሉ በፊት በዙሪያው ያለውን ነገር ጠንቅቆ የሚያነብ ሲሆን÷ በግንዛቤውና በግሩም ንክኪው በጨዋታው ልዩነት ይፈጥራል።
ባለፉት ዓመታት በተንታኝነት ሲያገልግል የነበረው ፖል ስኮልስ በኦቲዝም ሕመም የሚሰቃየውን ልጁን ለመንከባከብ ሲል በቅርቡ የተንታኝነት ስራ ማቆሙን ማሳወቁ ይታወሳል።
በእግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ምርጥ የመሐል ሜዳ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ፖል ስኮልስ በፈረንጆቹ 1974 በዛሬዋ ቀን ነበር የተወለደው።
በወንድማገኝ ጸጋዬ